የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት አስጠነቀቀ

ሰላምና መረጋጋትን ለማድፍረስ በሚንቀሳቀሱና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን እያስፈራሩ ነው ያላቸው ኃይሎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ሴክሬቴሪያት ዛሬ ባወጣው መግለጫ እስጠነቀቀ።
”የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከወጣ ወዲህ የፀጥታ ኃይሎች ባደረጉት እንቅስቃሴና በህዝቡ ተሳትፎ ከሞላ ጎደል በሁሉም የሃገራችን አካባቢዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የተረጋጋ ሰላማዊ ሁኔታ ለመፍጠር ተችሏል” ይላል መግለጫው።
ነገር ግን ”በነቀምትና ደምቢዶሎ ከተሞች ህገ-ወጥ ኃይሎች የሕዝቡን ሰላምና መረጋጋት ለማደፍረስ ጥረት ከማድረግ ባሻገር በፀጥታ ኃይሎች ላይ የእጅ ቦምብ በመወርወር አደጋ ለማድረስ እንቅስቃሴ አድርገዋል” ሲል አጋጥሟል ያለውን ችግር አስቀምጧል።
የፀጥታ ኃይሎች ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተቻለ መጠን የሰው ህይወት እንዳይጠፋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መመሪያ እንደተሰጣቸው የሚገልፀው መግለጫው፤ ”ይሁን እንጂ እነዚህ ኃይሎች ከዚህ የጥፋት ድርጊታቸው የማይቆጠቡ ከሆነ አስፈላጊ እርምጃ እንዲወስዱ” ለፀጥታ ኃይሎቹ ትእዛዝ መሰጠቱን አመልክቷል።
በተጨማሪም የኦሮሚያ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በተለያየ መንገድ ማስፈራሪያ እየደረሳቸው መሆኑን በተደጋጋሚ አቤቱታ እንዳቀረቡ የጠቀሰው መግለጫው፤ ይህ ድርጊት በቸልታ እንደማይታለፍና ክትትል በማድረግ ህጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን አስጠንቅቋል።
በሃገሪቱ ለሁለተኛ ጊዜ የካቲት 09/2010 ዓ.ም በመላው ሃገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተደነገገ በኋላ ከአስር ቀናት በላይ ሲሆነው በተወካዮች ምክር ቤት እስካሁን ውሳኔ አልተሰጠበትም።
በእረፍት ላይ የነበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፊታችን አርብ የካቲት 23/2010 ለአስቸኳይ ስብሰባ የተጠራ ሲሆን በዚሁ ስብሰባ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ለተያያዥ ዘገባዎች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *