ቆቦ ውስጥ በርካቶች መታሰራቸው እየተነገረ ነው

ባለፉት ሦስት ቀናት በሰሜን ወሎ ዞን በምትገኘው የቆቦ ከተማ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በተቀሰቀሰ ግጭት ህይወት ማለፉ እና ንብረት ላይም ጉዳት መድረሱ የሚታወስ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት ግን ከተማዋ አንፃራዊ መረጋጋት እንደነበራት ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ካለመረጋጋቱ ጋር ተያይዞም በትናንትናው እና በዛሬው ዕለት በርካቶች እየታሰሩ መሆኑን በስልክ ያነጋገርናቸው የከተማዋ ኗሪዎች ገልፀውልናል።
ባለቤታቸው ዛሬ ጧት እንደታሰሩ የነገረሩን የከተሟዋ ኗሪ ወደስድሳ የሚሆኑ የከተማዋ ኗሪዎች ወደፖሊስ ጣብያዎች ሲወሰዱ መመልከታቸውን ይናገራሉ።
በትናንትናው እና በዛሬው ዕለት የታሰሩትን የከተማዋ ነዋሪዎች ቁጥር ወደሁለት መቶ የሚያደርሱት ወይዘሮዋ፤ ባለቤታቸው በየትኛውም ዓይነት ተቃውሞ እንዳልተሳተፉ ከዚያ ይልቅ ለመታሰራቸው ምክንያት የሆነው የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ አባል ስለነበሩ መሆኑን ይናገራሉ።
ስማቸው መገለፁን ያልፈለጉት ወይዘሮ ለባለቤታቸው ውሃ ይዘው ፖሊስ ጣቢያ ባቀኑበት ወቅት “ለእርሱ ውሃ አያስፈልገውም” ተብለው መመለሳቸንም ጨምረው ለቢቢሲ ገልፀዋል።
የቆቦ ከተማ ኮምኒኬሽን ቢሮ የቡድን መሪ የሆኑት ወይዘሮ ሸዋዬ አሸብር በርካታ ወጣቶች በትናንትናው ምሽት መታሰራቸውን ለቢቢሲ የተናገሩ ሲሆን ትክክለኛ ቁጥራቸውን ግን እንደማያውቁ ገልፀዋል።
በርካታ የታሳሪ ቤተሰቦች በመከላከያ ሰራዊት፣ በፌዴራል ፖሊስ እና ከአካባቢው በተውጣጣ የፀጥታ ኃይል ወደሚጠብቁት ቦታ ታሳሪዎችን ጥየቃ ማቅናታቸውን ወይዘሮ ሸዋዬ ጨምረው ተናግረዋል።
የቡድን መሪዋ እንደሚሉት ከተማዋ ሙሉ በሙሉ ወደወትሮ እንቅስቃሴዋ ባትመለስም፤ በዛሬው ዕለት የፀጥታ ችግርን ያላስተናገደችም። በከተማዋ መጠነኛ የመጓጓዣ እንቅስቃሴ እንደነበረ ለመረዳት ችለናል።

ለተያያዥ ዜናዎች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *