የሳዑዲው ልዑል ሚተብ ቢን አብዱላህ ከእስር ተለቀቁ

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ከሶስት ሳምንት በላይ በቁጥጥር ስር የነበሩት የሳዑዲው ልዑል ሚተብ ቢን አብዱላህ መለቀቃቸውን ባለስልጣናት ገለጹ።

በአንድ ወቅት ለሃገሪቱ ንግሥና ተፎካካሪ ተደርገው ይወሰዱ የነበሩት ልዑል ሚተብ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ “የሥምምነት ክፍያ” ለመፈጸም ከባለሥልጣናት ጋር ተስማምተው ነው የተለቀቁት።

ልዑሉ ከሶስት ሳምንት በፊት በፀረ-ሙስና ዘመቻ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ከ200 በላይ የፖለቲካና የንግድ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው።

ሶስት ሌሎች ሰዎችም ከሳዑዲ መንግስት ጋር ከስምምነት ደርሰዋል።

“ልዑል ማተብ ማክሰኞ ጠዋት በትክክልም ተለቀዋል” ሲሉ ለመንግሥት ቅርበት ያላቸው ምንጭ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ አስታውቀዋል።

ሳዑዲን በመምራት ላይ የሚገኙት የልዑል ሞሃመድ ቢን ሳልማን የወንድም ልጅ የሆኑት ልዑል ማቲብ በፀረ-ሙስና ዘመቻው በቁጥጥር ስር ከዋሉትና በሃገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ተፅእኖ ካላቸው የንጉሳዊያን ቤተሰብ አባላት አንዱ ናቸው።

ልዑሉ የሃገሪቱ ብሔራዊ ጥበቃ የበላይ በመሆን አገልግለዋል።

የቀድሞው የሃገሪቱ ንጉሥ አብደላህ ልጅ የሆኑት የ64 ዓመቱ ልዑል ማተብ በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው በፊት ነበር ከስልጣናቸው እንዲለቁ የተደረጉት።

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ልዑላን፣ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የንግድ ሰዎች በቅንጡ ሆቴል ውስጥ ነው የሚገኙት።

የተጠርጣሪዎቹን የግል አውሮፕላኖች ጨምሮ አንዳንድ ሃብቶቻቸው እንዳይንቀሳቀስ እገዳ ተጥሎበታል።

ግንባር ቀደም ነዳጅ አምራች በሆነችው ሳዑዲ አረቢያ ሙስና የተስፋፋ ሲሆን የንግድ እንቅስቃሴው አካል ተደርጎም ይወሰዳል።

ልዑል ሞሃመድ ሃገሪቱ በዚህ ረገድ ለውጥ እንደሚያስፈልጋት በመግለፅ ትኩረታቸውን በሃገሪቱ ባለሃብቶች ላይ አድርገዋል።

ብዙዎቹ የሃገሪቱ ዜጎች የፀረ-ሙስና እንቅስቃሴው የሃገሪቱን ሃብት ለሁሉም ዜጎች ለማዳረስ ይረዳል በሚል ለውጡን በጸጋ ተቀብለውታል።Read more

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *