የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ግዴታ የማን ነው?

‘ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይረገሰስ በህይወት የመኖር፤ የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት አለው’ ይህ የሰፈረው በኢፌድሪ ህገ-መንግሥት አንቀፅ 14 ላይ ነው።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል በተነሱ ተቃውሞዎች የብዙዎች ሕይወት ጠፍቷል፤ ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ክልሎች መካከል ብሔርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችም ተነስተው በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀል፤ ንብረት መውደም እንዲሁም ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት ሆኗል።
ከነዚህም ውስጥ ከደቡብ ክልልና ከቤኒንሻንጉል ጉሙዝ የተፈናቀሉ የአማራ ብሔር ተወላጆች፤ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች እንዲሁም ከጎንደር የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆችን መጥቀስ ይቻላል።
በተለያዩ ክልሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በተነሱ መሰል ግጭቶች የመማር ማስተማር ሂደት እስከመስተጓጎል ደርሷል።
በሃገሪቱ ውስጥ በሚፈጠሩ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች የተነሳ ብዙዎች ስጋታቸውን ለቢቢሲ ሲገልፁ ቆይተዋል። የበርካቶች ቅሬታ የመንግሥት ተቋማት የዜጎችን መብት በማስጠበቅ ፋንታ “እየጣሱ” መሆኑ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። በፌስቡክ ገፆቻችን ከሰበሰብናቸው አስተያየቶች መካከል “ሕገ መንግሥቱ በግልፅ ተጥሷል፤ ሃገሪቱን እየመራ ያለው ኢህአዴግ ደህንነት እንዳይሰማን እያደረገው ነው ያለው” የሚሉ ይገኙበታል።
በሌላ በኩል በክልሎች እየታየ ያለው የፀጥታ ስጋት የፌደራል መንግሥት ችግሩን ለክልሎች ብቻ መተዉና ኃላፊነቱ በአግባቡ ያለመወጣቱ ውጤት ነው የሚልም ቅሬታና ትችትም ይደመጣል። “የፀጥታ ጉዳይ ለክልሎች የሚተው ነገር አይደለም። የፌደራል መንግሥት በክልሎች ያለውን ስርዓት አልበኝነት መቆጣጠር አለበት” በማለት።
ህገ-መንግሥቱና የዜጎች መብት?
በኤፌድሪ ህገመንግስቱ አንቀፅ 32 (1) “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሀገር የመውጣት ነፃነት አለው” ይላል።
አንቀፅ40 (1) ደግሞ “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የመሰማራት፤ ለመተዳደሪያው የመረጠውን ስራ የመስራት መብት አለው” ይላል።
በተጨማሪም በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 13 ላይ ዜጎች ከሀገሪቱ የመንግሥት አካላት ማግኘት ስላለባቸው መሰረታዊ መብቶች ይዘረዝራል። የመኖር መብት፣ የአካል ደህንነት መብቶች፣ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቶች እንዲሁም ንብረት የማፍራትና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ይጠቀሳሉ።
በዚሁ አንቀፅ ንኡስ አንቀፅ አንድ ላይም በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ የፌደራል መንግሥትና የክልል ህግ አውጪ፣ ህግ አስፈፃሚና የህግ ተርጓሚ አካላት እነዚህን መብቶች እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ ኃላፊነትና ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
እነዚህ መብትና ግዴታዎች በክልል ሕገ-መንግሥቶች ላይም በድጋሜ ተረጋግጠዋል፡፡ በሀገር ውስጥ ለመዘዋወር ደግሞ ፓስፖርት ወይንም የመኖሪያ ፈቃድ አያስፈልግም፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆን ብቻውን በቂ እንደሆን ሀገመንግሥቱ ያረጋግጣል።
እነዚህ መብቶች በሌሎች እንዳይጣሱ የማስከበር ግዴታ ያለበት መንግሥት መሆኑን የህግ ሙሁርና በፌዴራሊዝም ስርዓት ምርምር ያደረጉት አቶ ውብሸት ሙላት ለቢቢሲ ይናገራሉ። “የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት ሲጣስ ወይንም እክል ሲፈጠር፣ በተጨማሪም ከተሰማሩበት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት የሆኑ ሰዎችን ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ በፍርድ ቤት ማስወሰን ይቻላል” ይላሉ።
“ዜጎች የፍትሕ ተቋማትን እንዲጠቀሙ ድጋፍ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ያለው የፍትሕ ተቋማት አወቃቀር ለዜጎች መተማመኛ ይሆናል ማለት የሚቻል አይመስልም፡፡” ይላሉ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶችና ድንጋጌዎች መርሆች ጋር በተጣጣመ መንገድ እንደሚተረጎሙም ይናገራሉ።
የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ
በህገ-መንግስቱ መሰረት መንግስት የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች የማክበርን እና የማስከበር ግዴታ ተጥሎበታል።
አቶ ውብሸት እንደሚሉት፥ በተለይ ብሔርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች በሚነሱበት ወቅት የግለሰቦችን ሰብዓዊ መብት የማስከበር ግዴታ የሁለቱም መንግስት መዋቅሮች ግዴታ ነው።
”ነገር ግን ህገ-መንግሥቱን በማስፈፀም ደረጃ የተቋማት ችግር አለ። ምክንያቱም አንዳንድ ግጭቶች የብሔር መልክ ሲኖራቸው የግለሰቦች መብትና ደህንነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል” ይላሉ።
“በአንድ ክልል ውስጥ የሚኖር አንድ ብሔረሰብ በክልሉ መንግስትና ተቋማዊ አስተዳደር በደል ተፈፅሞብኛል ቢል አቤቱታውን የሚያቀርበው ለማን ነው?” በማለትም ይጠይቃሉ።
እንደ ምሳሌም ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የተፈናቀሉ አማሮች፤ ጎንደር ላይ የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆች፤ በሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች በደል ተፈፅሞብናል ብለው ክሳቸውን የሚያቀርቡት የት እንደሆነም መታወቅ አለበት ሲሉ ይሞግታሉ።
“የአንድ ክልል መንግሥት ወይም የክልል ተቋማዊ አስተዳደር ክስ ቀርቦበት የዚየው ክልል መንግሥት አጣሪ እና ፈራጅ ከሆነ የሕገ-መንግሥት ክፍተት እንዳለው የሚያሳይ ነው” በማለት አቶ ውብሸት ይናገራሉ።
በእኔ እምነት፥ ይህ ክፍተት ሊፈታ ይችል የነበረው በፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው። “ሆኖም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አወቃቀር ገለልተኛ አቋም እንዲይዝ አልተደረገም” በማለት ወደ ግማሽ የሚሆኑት የምክር ቤቱ አባላት ከሁለት ክልል ብቻ የተውጣጡ መሆናቸውን በመግለጽ ጨምረው ያስረዳሉ።
መፍትሄ?
“ችግር ፈጣሪዎቹ ባለሥልጣናት ከሆኑ፣ ዞሮ ዞሮ በመንግሥት ተቋም ውስጥ ስላሉ መንግሥት የዜጎችን መብት ማክበር ግዴታው ነው፡፡ ሌሎች ሰዎች የእነዚህን ዜጎች መብት ሲጥሱ የማስከበር አሁንም ግዴታ አለበት፡፡” የሚሉት ኣቶ ውብሸት፥ “እንደነዚህ ዓይነቶቹን የመብት ጥሰቶች የፖለቲካ አንድምታቸው ላይ ከማተኮር ይልቅ ግለሰባዊ ማድረግ፣ መፍትሔያቸውንም በፍርድ ቤት በኩል እንዲሰጥ ማድረግ መቻል አለብን፡፡” ይላሉ።
“መንግሥትም ይሄንን አካሄድ ማበረታታት ሲገባው ፖለቲካዊ መፍትሔ በመስጠት ተጠምዶ ኖሯል” የሚሉት አቶ ውብሸት መፍትሄው ግን የፍትሕ ተቋማትን ገለልተኛ እንዲሆኑ በማደረግ ሕጋዊነትን እና የሕግ የበላይነትን ማስፈን እንደሆነ ይናገራሉ።
በተለይ ብሔርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች በሚነሱበት ወቅት የፌዴራል መንግሥት ልዩ ትኩረት በመሥጠት በበላይነት ሊቆጣጠርና ሊያያቸው እንደሚገባ አቶ ውብሸት ይናገራሉ።
“በተቻለ መጠን ከሳሾቹ ከአጣሪው አካል እንዲሁም ዳኝነቱን ከሚሰጡት አካላት በብሔር ሊለያዩ ይገባል። ይህ ግን ጊዜያዊ መፍትሄ ነው” የሚሉት አቶ ውብሸት ዘላቂ መፍትሄ መሆን ያለበት “የየትኛውም ብሔር አካል ሆነ ግለሰብ ግለሰባዊ መብቱ መጠበቅ አለበት” ይላሉ።
ህገ መንግስት ጥናት ያደረገው የህግ ባለሞያው አቶ ኤፍሬም ታምራት ግን ከዚህ የተለየ አስተያት ኣለው። በፌዴሬሽን ምክር ቤት ፍትሃዊ የሆነ ውክልና እንዳለና የህገ መንግስት አተረጓጎም ስህተት ሲኖር ብቻ ወደ ምክር ቤቱ እንደሚኬድ ይናገራል።
“ለአብነትም ከዓመታት በፊት፥ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተከስቶ የነበረው የብሄር ግጭት መክር ቤቱ ፍትሃዊ የሆነ ውሳኔ መስጠቱ አመላካች ነው” ይላል።
እንደ አቶ ኤፍሬም ገለፃ ከሆነ፥ ማናቸውም የግለሰብም ይሁን የቡድን የመብት ጥሰቶች ከክልል እስከ ፌዴራል በተዘረጉ የህግ መዋቅሮች በወንጀል ህግ መዳኘት ይኖርባቸዋል።

ለተጨማሪ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *