የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር 40, 000 የሚጠጉ አፍሪቃውያን ስደተኞችን በግዳጅ እንደሚያባሩ ተናገሩ

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር 40, 000 የሚጠጉ አፍሪቃውያን ስደተኞችን በግዳጅ እንደሚያባሩ ተናገሩ

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ቢሮ እስራኤል በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪቃውያን ስደተኞች ያለፍላጎታቸው የመመለስ አሊያም ወደ እስር ቤት የማስገባትን ውሳኔ እጅግ እንዳሳሰበው ገለጸ።

የአገር ውስጥ ሚንስትር ቢሮ ከደህንነት ሚንስትር ቢሮ ጋር በመተባበር ወደ 40, 000 የሚጠጉ አፍሪቃውያንን ከእስራኤል በግዳጅ በማስወጣት ወደ ሌላ 3ኛ የአፍሪቃ አገር የማስፈር እቅድ ማዘጋጀቱ ይታወሳል።

ስደተኞቹ ያለፍቃዳቸው እንዲሰፍሩ ለማድረግ የታሰበችው 3ኛ አገር ሩዋንዳ መሆኗን ከሚወጡት መረጃዎች ለመረዳት ተችሏል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ይህ እቅድ ወደ 40, 000 የሚጠጉ አፍሪቃውያን ስደተኞችን ያለ ፍቃዳቸው ከእስራኤል ለማስወጣት የሚረዳ አሳማኝ መፍትሄ ሆኖ እንዳገኙት እና የአለም አቀፍ ድጋፍም እንዳገኙ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህ ውሳኔ ስደተኞችን ከእስራኤል የማጽዳት 3ኛው ደረጃ እንደሆነ አብራርተዋል። የመጀመሪያው በግብጽና በእስራኤል አዋሳኝ ስደተኞን ከመግባት የሚገድብ ግንብ መስራት እንደነበረ ያስታወቁት ጠቅላይ ሚንስትሩ በ2ኛ ደረጃ ወደ 20, 000 ስደተኞችን የማባረሩ ሂደት እንደነበረ አሳውቀዋል።

በዚህ በአሁኑ ውሳኔ ላይ ትብብር የማያደርጉ ስደተኞችን ላልተወሰነ ጊዜ ወደ እስር ቤት እንደሚላኩና፤ ስደተኛ ካምፑን ለመጠበቅ የተመደበውን ሃይል ለሌላ አገራዊ ደህንነት ማዋል አለብን በማለት ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል።

እንደ ሪፖርቶች ዘገባ መሰረት በእስራኤል የፓለቲካ ጥገኝነት ከሚጠይቁ አፍሪቃውያን ስደተኞች መካከል በብዛት የሱዳንና የኤርትራ ዜጎች እንደሚገኙበት ለመረዳት ተችሏል።

የአፍሪቃ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በተመለከተ እስራኤል ልትተገብረው ያቀደችው ይህ እቅድ በአለም አቀፍ ደረጃ ድጋፍ ማግኘቱ በተባበሩት መንግስታት ስጋትን ሲጭር በብዙዎች አነጋጋሪ ሆኗል።

እስራኤላውያን በአለም ተበታትነው በስደት መኖራቸውን የቅርብ ታሪክ መሆኑን በማስታወስ ይህንን በግዳጅ 40,000 አፍሪቃውያን ስደተኞችን ወደ ሌላ 3ኛ አገር የማስፈር አሊያም በእስር ቤት የማጎር ውሳኔን የሚተቹም ተገኝተዋል።Read more

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *