ካይሮ፤ አልሲሲ ኢትዮጵያን በድጋሚ አስጠነቀቁ

የግብጹ ፕሬዝዳንት አብደል ፈታህ አልሲሲ ኢትዮጵያን በተዘዋዋሪ ነገር ግን በጥብቅ በድጋሚ አስጠነቀቁ፡፡ አልሲሲ ማስጠንቀቂያውን የሰጡት ኢትዮጵያ ከምታስገነባው የህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ የግብጹ ፕሬዝዳንት ዛሬ በቴሌቪዥን በሰጡት አስተያየት «ውሃ የህይወት እና ሞት ጉዳይ» እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አልሲሲ ከሳምንት በፊት በወቅታዊ አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫም ተመሳሳይ ገለጻ ተጠቅመው ነበር፡፡ በወቅቱ “ለእኛ ውሃ የብሔራዊ ደህንነት ጥያቄ ነው፡፡ ሀገራዊ ደህንነታችንን የማስጠበቅ አቅሙ ደግሞ አለን” ሲሉ “በተዘዋዋሪ ለኢትዮጵያ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ ነው” የተባለለትን ኃይለ ቃል ሰንዝረው ነበር፡፡ የአልሲሲ የዛሬው አስተያየት የተደመጠው ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በአማካሪ ድርጅት አማካኝት የቀረበላቸውን የመነሻ ጥናት ባለፈው ሳምንት ሳያጸደቁ ከተለያዩ በኋላ እንደሆነ አሶሴትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ በኢትዮጵያ እና በሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ስምምነት የተቀጠረው የፈረንሳይ አማካሪ ድርጅት የህዳሴው ግድብ በግብጽ እና ሱዳን ላይ የሚያስከትለውን ተጽእኖ እያጠና ይገኛል፡፡ ግብጽ የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ ወደ ሀገሯ የሚፈስሰውን የውሃ መጠን ይቀንሰዋል የሚል ስጋት ቢኖራትም ኢትዮጵያ በበኩሏ የግድቡ ግንባታ “ትርጉም ያለው ተጽእኖ” እንደማያስከትል በተደጋጋሚ ማረጋገጫ ስትሰጥ ቆይታለች፡፡ የአልሲሲ የዛሬው አስተያየት “ግብጻውያንን ለማረጋጋት የታለመ ነው” ተብሎለታል፡፡

መረጃውን ያገኘነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *