የፍልስፍና ሊቁ ሰሎሞን ደሬሣ አስከሬንን የማቃጠል ሥነ ስርዓት ዛሬ ይከናወናል!

 የፍልስፍና ሊቁ ሰሎሞን ደሬሣ አስከሬንን የማቃጠል ሥነ ስርዓት ዛሬ ይከናወ

አንጋፋው ገጣሚ፣ ጋዜጠኛ፣ የፍልስፍና ሊቅና መምህር ሰሎሞን ደሬሣ፤ ከትላንት በስቲያ ጥቅምት 23 ቀን 2010 ዓ.ም በሚኖርበት አሜሪካ ሚኒሶታ በ80 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየ ሲሆን አስክሬኑ በኑዛዜው መሠረት በዛሬው እለት ይቃጠላል ተብሏል፡፡
ሰሎሞን ደሬሣ ከሰባት ወራት ህመም በኋላ በሚኒሶታ ሚኒያፖሊስ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ቤተሰቦቹ በተሰበሰቡበት ህይወቱ ማለፉ ታውቋል። ለህልፈት ያበቃውም የልብ ህመም ነው ተብሏል፡፡
በህመም ምክንያት ሥራውን እስካቆመበት ጊዜ ድረስ በሚኒሶታ ዩኒቨርሲቲ፣ የሃይማኖቶች ንፅፅር የፍልስፍና መምህር ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡
ከእናቱ ከወ/ሮ የሺመቤት ደሬሣ፣ ከአባቱ ከአቶ ደሬሣ ላንኪ በቀድሞ የወለጋ ጠቅላይ ግዛት ጊምቢ አውራጃ ውስጥ በምትገኝ ጩታ ቀበሌ ነው የተወለደው- ሰለሞን ደሬሳ፡፡
የሀሳብና የፍልስፍና ሰው የሆነው ሰለሞን፤ የዓለም ሃይማኖቶችን በሙሉ በሚገባ ያጠና ምሁርና መምህር መሆኑን ታናሽ ወንድሙ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የባላደራ መስተዳድር ከንቲባ የነበሩት ብርሃነ ደሬሳ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡
በዚህ የፍልስፍና ህይወቱም “ብቻዬን እንደመጣሁ ብቻዬን ነው የምሄደው” የሚል አስተሳሰብ የነበረው ሰለሞን ደሬሳ፤ በሚከተለው እምነት መሰረት፣ አስክሬኑን ዛሬ ቅዳሜ ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም የማቃጠል ሥነስርዓት ይካሄዳል፡፡
ሰለሞን ደሬሳ በጋዜጠኝነቱ “አዲስ ሪፖርተር” የሚባል መፅሄት ከገዳሙ አብርሃም ጋር ያሳትም የነበረ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች ላይም ጽሁፎችን ያሳትም እንደነበር አምባሳደር ብርሃነ ገልፀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም “ዘበት እልፊቱ- ወለሎታት” እና “ልጅነት” የሚሉትን የግጥም መድብሎች ጨምሮ ሶስት መፅሃፍትን ለንባብ አብቅቷል፡፡
ሰለሞን ደሬሳ በታይላንድ ባንኮክ ነዋሪ የሆነች ገላና ደሬሳ የምትባል የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነበር።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *