ኦሮሚያ ዳግም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ተዳረገች

  • በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ የኦሮሚያን ክልላዊ መስተዳድር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዳግም ሰለባ እንድትሆን ያደረጋት መሆኑ ተገለጸ።

ከአስር ወሩ ሀገር አቀፍ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳት ሶስተኛ ወር ላይ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ዳግም የተቀጣጠለው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ሕወሐት መራሹ ስርዓት የተናጠል የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ እንዲያውጅ ያስገደደው መሆኑን ተንታኞች እየገለጹ ሲሆን የተነሳውን ሕዝባዊ እምቢተኝነትና አልገዛም ባይነት በወታደራዊ ሃይል ለመጨፍለቅ መጣር መፍትሄም የሚሆን አማራጭ ግን አይደለም ይላሉ።

በኦሮሚያ ክልል የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በክልሉ የኮማንድ ፖስት ተቋም ማቋቋሙን ይፋ ያደረገ ሲሆን በበላይነት የሚመራውም በብሔራዊ የስለላ ድርጅቱ መሪ ኢሳይያስ ወልደጊዮርጊስ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር አሰፋ አቢይ፣ የማእከላዊው ረታ ተስፋዬና ከመከላከያ ጄ/ል ገብሬ ዲላ ኮሚቴ መሰል መዋቅር እንደሚመራ ለማወቅ ተችሏል።

በኮማንድ ፖስቱ ውስጥ በአዛዥነት ከተገለጹት ውስጥ የመከላከያው ደህንነት ክፍል ሃላፊ ጄ/ል አብርሃ ካሳ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር ኢተፋ ቶላ እና የደህንነቱ ሃላፊ ደመላሽ ገብረአምላክ በኮማንድ ፖስቱ ውስጥ በአዛዥነት የተጠቀሱ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ሕወሐት መራሹ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት በውስጣዊና ውጫዊ ዓመጽ እየተናጠ ያለና የፌዴራሉም ስርዓት እየተሰነጣጠቀ መሆኑን ክስተቶቹ እያሳዩ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ኦሮሚያ ክልልን በተናጠል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ለማዋል የቻለው በክልሉ ከተነሳው ህዝባዊ እምቢተኝነት ሃይል ጎን ለጎን በክልሉ ድርጅት በኦህዴድ በኩል በተነሳው ዓመጽ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል።

የኢህአዴግ አካል የሆነውና የኦሮሚያን ክልል እያስተዳደረ ያለው የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት [ኦህዴድ] ከስርዓቱ አስኳል ከሆነው ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ [ሕወሐት] ጋር ከፍተኛ ግብግብ እያደረገ መሆኑ የታወቀ ሲሆን የድርጅቱ አንጋፋ መስራችና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ የነበሩት አቶ አባዱላ ገመዳ “በሕዝቤና በድርጅቴ ላይ እየደረሰ ባለው በደል ምክንያት የፌዴራሉን ስልጣኔን በመልቀቅ ለመታገል ወስኛለሁ” በማለት መግለጻቸው ይታወሳል።

የኦህዴድ ከፌዴራሉ ስርዓት በተለይም ከሕወሐት የበላይነት ለመለቃቅ ማመጽ በኦሮሚያ ክልል የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ እምቢተኝነት ለመቋቋም አቅም ስላነሰው ኦሮሚያን በተናጠል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ለማዋል እንደቻለ መረዳት ተችሏል።

በኦሮሚያ ክልል የተቀጣጠለው ህዝባዊ እምቢተኝነት ሰሞኑን በኦሮሚያ አቀፍ እየተካሄደ ሲሆን በርካታ ሰዎችም ህይወታቸውን በግፍ ሲገደሉ ተስተውሏል።

ህዝባዊ እምቢተኝነቱ ስር ከሰደደው ሙስና፣ የንብረትና መሬት ዘረፋ፣ በግፍ እየተሰቃዩ ያሉ የፖለቲካ እስረኞች ጉዳይና በሀገሪቱ በተንሰራፋው የመልካም አስተዳደር መጥፋት ምክንያት እንደሆነ ህዝቡ ደጋግሞ ቢገልጽም በስርዓቱ በኩል የህዝቡን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ በሃይልና በመሳሪያ ተጠቅሞ ለመጨፍለቅ በመፈለጉ የአስቸካይ ግዜ አዋጅን እያከታተለ ሲያውጅ ለማየት ተችሏል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *