መከላከያና ፌዴራል ፖሊስ በነገው እሬቻ ክብረ በዓል ላይ ሰራዊት አሰማራለሁ አለ

በወንድወሰን ተክሉ

በነገው እሁድ ጥቅምት 1 ቀን በሚከበረው ዓመታዊ የእሬቻ ክብረ በዓል ላይ የፌዴራሉ ፖሊስ ሃይልና መከላከያ ወታደር እናሰማረለን በማለት ከአባገዳ መሪዎች ጋር የተደረገውን ስምምነት በመጣስ መግለጫ አወጣ።

በኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድርና በአባገዳ መካከል የተካሄደውን ስምምነት የፌዴራሉ መከላከያ፣ ፖሊስ ሃይልና የደህንነት ቢሮ ተስማምቻለሁ በማለት በነገው ክብረበዓል ላይ የታጠቀ ሰራዊት እንደማያሰማሩ ገልጸው የነበረውን ቃል በመሻር ቢሾፍቱ የኢዮጵያ ዓየር ሃይል ካምፕ ያለበትና ሌላም ወታደራዊ ተቋማት ያሉባት ከተማ በመሆኗ ከ3 እስከ 5 ሚሊዮን የሚሰበሰብን ህዝብ ዝም ብለን ለፎሌዎቹ እና ለክልሉ ያልታጠቀ ፖሊስ በመተው አንቀመጥም በማለት የታጠቀ ሰራዊት አካባቢውን እና ሕዝቡን በርቀት እንዲጠብቅ አዘናል የሚል መግለጫ ከረፋፈደ በኋላ ለማውጣት ችለዋል።

አቶ ታከለ ደንሳ እና አቶ በየነ ሰንበቱ ዓርብ ምሽት ላይ ለቪ.ኦ.ኤ አማርኛ ክፍል እንደተናገሩት “ይህ የመንግስት የመጨረሻ ደቂቃ ላይ የተነገረን ውሳኔ ቀደም ሲል የእኛ አባገዳዎችና የኦሮሚያ ክልል መስተዳድር ባለስልጣናት ከመከሩበትና ከተስማሙበት ነጥቦች የተለየ እና አዲስ ነው” ያሉ ሲሆን መንግስት ቀደም ሲል በዓሉ የጦር መሳሪያ በታጠቀ መከላከያ ሰራዊት የሚጠበቅ ሳይሆን በሲቪል ለባሽ ወጣቶች/ፎሌዎች/እና በኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ሃይል መሳሪያ ሳይታጠቁ የሚደረግ ጥበቃ ነው ያለውን ስምምነቱን የሚጥስ ሆኖ አግኝተነዋል።

በኦሮሚያ አባገዳዎች በኩል በበዓሉ እለት ስነስርዓት የሚያሲዙ ፎሌ እየተባሉ የሚጠሩ ወጣቶችን ማዘጋጀታቸውን ገልጸው በእለቱ በበዓሉ ላይ ከመንፈሳዊ ንግግር፣ ጸሎትና ምርቃት በስተቀር አንዳችም ፖለቲካዊ ንግግሮችም ሆነ መፈክሮች እንደማይካሄዱ በመግለጽ ህዝቡ በነጻነትና በመንፈሳዊነት አከባበር እንዲያከብር መንግስት የታጠቀም ሆነ ያልታጠቀ ሰራዊት እንዳይመድብ ጠይቀን ተቀባይነትም አግኝተናል ማለታቸው ይታወቃል።

በ2016ቱ ዓመታዊው የእሬቻ ክብረ በዓል ላይ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎችና ወታደሮች በተተኮሰ ጥይት ከ700 በላይ ንጹሃን ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን ገሚሶቹም ከላይ በሄሊኮፕተር ከታች በምድር በታንክና በአስለቃሽ ጋዝ ከሚተኮስባቸው ለማምለጥ ሲጋፉ በአከባቢው ተቆፍሮ በነበረ ጉድጋድ ውስጥም እየገቡ ህይወታቸው ያለፈ በርካቶች እንደሆኑ አይዘነጋም።

በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ከሳምንታት በፊት ቀደም ብለው መንግስት በዘንድሮው የእሬቻ ክብረ በዓል ላይ ወታደር እንዳያሰማራ ሲጠይቁና ሲያስገነዘቡ የቆዩ ሲሆን የኦሮሚያ አባገዳዎችም መጨረሻ ላይ ከክልሉ ባለስልጣናት ጋር በመደራደር መንግስት በእለቱ ምንም ወታደር ላያሰማራ ከስምምነት ላይ ደርሰናል ብለው ቢገልጹም በበዓሉ ዋዜማ ቀን መንግስት ስምምነቱን በመሰረዝ ያልተፈለገውን ሰራዊት እንዲሰማራ ማዘዙን ለማወቅ ተችሏል።

የእሬቻ ክብረ በዓል በኦሮሞ ማህበረሰብ በየዓመቱ በታላቅ ድምቀት የሚከበር መንፈሳዊና ባህላዊ ክብረ በዓል ሲሆን ነገ እሑድ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ሀይቅ ከመላው ኢትዮጵያና ከውጭም የመጡ የኦሮሞ ተወላጆች በጠዋት ተገኝተው በአባገዳው መሪነት ምስጋና፣ አምልኮ፣ ምርቃት፣ ልመና/አምላክን/እና ለሟቾችም የንሰሀ ጸሎት በማድረግ የሚከበር ዓመታዊ በዓል እንደሆነ ለማወቅ የተቻለ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ይታደምበታል ተብሎም ይጠበቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *