ብአዴን ቢታደስ!

ጌታቸው ሽፈራው

ትህነግ( ህወሃት) ገና ከመፈጠሯ ጀምሮ በርካታ የውስጠ ድርጅት ፈተናዎች አጋጥመዋታል። በተለይ የመጀመሪያዎቹ የሰፈር ጠቦች ነበሩ። ጎጠኝነት ስትበቅል የተጠናዎታት በሽታ ነው። ትህነግ ከደደቢት በርሃ ጀምሮ በርካታ የውስጠ ድርጅት ፈተና ሲያጋጥማት “ተገማግመናል፣ ታድሰናል፣………” እያለች ጥያቄ ያነሱባትን ስታዘናጋ ቆይታለች።

ከ983 በሁዋላም ህዝብ ሲያምፅ፣ ካድሬዎች ሲያኮርፉ ” ተሃድሶ” እየተባለ ስልጣን ሲያራዝሙ ቆይተዋል። የዘንድሮውን ከቀደመው የሚለየውም የእስካሁኑ ” ግምገመና ተሃድሶ ምን ለውጥ አመጣ?” እንዳይባሉ “ጥልቅ” የምትል ቃል መጨመራቸው ብቻ ነው።

” ጥልቅ ተሃድሶ” የሚሉት ማዘናጊያ ዋና አላማውም ከእጃቸው አፈትልኮ የነበረው ስልጣንን እንዴት ማቆየት እንዳለባቸው፣ አመፅ የተቀሰቀሰበት አካባቢ ምን አይነት አፈና መደረግ እንዳለበት ከማስተማር ውጭ ወደ ህዝብ የሚያቀርብ አይደለም

ባለፈው አመት በአማራና ኦሮሚያ ክልል አስደንጋጭ አመፅ አጋጥሞት የነበረው ትህነግ ተሃድሶ እያለ ለአመፁ ቅርበት አላቸው ያላቸውን ካድሬዎችና ህዝብ ላይ አፈናውን ማክበድ ነው። ኦህዴድና ብአዴን ከትህነግ ውጭ ማንም አዳኝ እና ቀጭ እንደሌላቸው ማስገንዘብ፣ ልካቸውን ማሳየት ነው።

እነ አዲሱ ለገሰ፣ በረከት ስምኦን…… ትህነግን (ህወሃትን) አባይን ለማሻገር በወኪልነት ያቋቋሙት ብአዴን ሰሞኑን ጥልቅ ተሃድሶ እያደረኩ ነው ብሏል። በእርግጥ ከአሁን በፊትም ተመሳሳይ ነገር ሲል ቆይቷል። ትህነግ ብአዴን ወክየዋለሁ የሚለውን ህዝብ በ”ትምክተኝነት” ሲፈርጅ ኖሯል። ብአዴንም በየጊዜው ትህነግ ባስቀመጠው መገምገሚያ መሰረት ወደ ህዝብ የተጠጉ የመሰሉትን ካድሬዎች ” የትምክተኝነት ዝንባሌ” ሰበብ ሲያሸማቅቅ፣ ከህዝብ ጎራ ወደ ትህነግ ጎራ እያስገባ “ታድሰናል!” እያለ ለትህነግ ሪፖርት ሲያደርግ ኖሯል።

ባለፈው አመት በተነሳው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ምክንያት ትህነግ መካከለኛውን የብአዴን ካድሬ ብቻ ሳይሆን እነ ገዱን ሳይቀር ህዝብን በሚያጥላላበት “ትምክህት” ጎራ መድቧቸዋል። ለትህነግ ብአዴን እንደ አለምነው መኮንን ህዝብ ላይ እየዳፈቀ፣ እንደ ደመቀ መኮንን ዳር ድንበርን ፈርሞ እየሸጠ፣ ………እንዲታዘዘው ይፈልጋል። የትህነግ ወኪል ሆኖ ከተፈረጀው ህዝብ ጎን መቆም የሚታሰብ አይደለም። የተፈረጀውን ህዝብ ከማስመታት ተቆጥቦ፣ ከመዝለፍ ታቅቦ መቀመጥ እንኳን ብአዴንን በትህነግ ያስወቅሰዋል። ታደስ፣ ተገምገም ይባላል። ወደ ድሮው ወኪልነትህ ተመለስ እንደማለት!

ብአዴን ጥልቅ ተሃድሶ አደረኩ ካለ በሁዋላ መቀሌ ድረስ ሄዶ ትህነግ እግር ተደፍቷል። የፈሰሰው ደም እያለ፣ ደም አፍሳሹን ትህነግ እግር መደፋት መታደስ መሆኑ ነው። ህዝብ ያለ አግባብ ተከልሎብኛል ያለውን መሬት አሳልፎ መስጠት፣ አማራና ቅማንት ብሎ ከፋፍሎ ለትህነግ አስሮ ማስደብደብ መታደስ ነው።

መታደስ የትህነግ ስልትና ፖሊሲ ነው። ወኪሎችን ከህዝብ አርቆ እሱ ስር እንዲልመሰመሱ የሚያደርግበት መቅጫ ስልት ነው። መታደስ ማለት ከህዝብ አቋምና ፍላጎት ርቆ ትህነግ አቋምና ፍላጎት ስር መመሸግ ነው። ተሃድሶ ህዝብን ለወኪል ማስበዝበዝና ማስገዛትን እንደ ፖሊሲ እንዳይበረዝ የሚሰጥ ስልጠና ነው።

ብአዴን ታደሰ ተብሎ እንዲኖረው የሚፈለገው የትህነግ አቋም፣ የትህነግ አስፈፃሚነት ነው። ከህዝብ መራቅ ብቻ አይደለም። ምራቁን ህዝብ ላይ መትፋትም ግዴታው ነው። ምክንያቱም ትህነግ ህዝቡን ፈርጆ ለማንቋሸሽ፣ ለማደህየትና ለመግደል ቆርጦ የተነሳ ቡድን ነው። ይህን የትህነግ አላማ የማያስፈፅም መታደስ ወይንም መወገድ ይገባዋል። በመሆኑም ብአዴን ታደስኩ ቢል ሊይዝ የሚችለው የትህነግን አቋም፣ የወኪልነቱን ተግባር ነው። ብአዴን ሲታደስ ሊያስቀጥል የሚችለው የእነ አለምነውን ስድብና ጥላቻ፣ የእነ ደመቀ ክህደት ነው። ትህነግ የሚፈልግበት ይህን ስለሆነ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *