በደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ይገነባል የተባለው የቴሌቭዥን ማሰራጫ ውዝግብ አስነሳ!

የደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያንን ተጠግቶ ለመገንባት የታሰበው የቴሌቭዥን ማሰራጫን በመቃወም አንድ የደብሩ አገልጋይ መታሰራቸውን ተከትሎ ባለፈው እሁድ (መስከረም 14 ቀን 2010ዓ.ም) የአካባቢው ነዋሪዎች ባሰሙት ተቃውሞ ከፖሊስ ጋር ተጋጩ። ይህንንም ተከትሎ አምስት የመኢአድ አባላትና በርካታ ወጣቶች መታሰራቸው ከፓርቲው የአዲስ አበባ ጽ/ቤት ጥቆማ ደርሷል።፤ የደብረታቦር ከተማ ከንቲባ አቶ ታደሰ ይርዳው በበኩላቸው፤ ችግሩን የቀሰቀሱት የቤተክርስትያኗ ምዕመናን ሳይሆኑ የፖለቲካ ተልዕኮ ያላቸው አካላት ናቸው  ብለዋል።

ለደብረታቦር ከተማና አካባቢዋ የቴሌቭዥን ስርጭት የአንቴና ተከላ ይሆናል ተብሎ ከቤተክርስቲያኗ ይዞታ ላይ የ1500 ካሬ ሜትር ቦታ ተጠይቆ ነበር የሚሉት ከንቲባው፤ ከአካባቢው ነዋሪዎች፤ ከሰበካ ጉባኤው እና ከቤተክርስትያኗ አመራሮች ጋር በመነጋገር ቀድሞ ከተወሰነው ቦታው እንዲቀየር ከመደረጉም ባለፈ የመንገድን የውሃ አገልግሎት ተሟልቶ ለቤተክርስቲያኗ ካሳ እንዲሰጥ መጠየቁንም አመልክተዋል። ከተደረሰው ስምምነት በኋላ በቤተክርስትያኑ ቅጥር ውስጥ የሚኖሩ አባ ብርሃን የተባሉ የቤተክርስቲያኗ አገልጋይ በግላቸው ድርጊቱን በመቃወም ችግሩ እንደተጀመረ ያስረዳሉ። እኚህን አባት ወዳልተፈለገ መንገድ የሚመራ አካል ከጀርባ አለ የሚሉት ከንቲባው፤ የከተማዋ ወጣቶችንም በገንዘብ በመደገፍ ወደዚህ ረብሽ እንዲገቡ ሆነዋል ሲሉ ይከሳሉ።

ባለፈው እሁድም የአባ ብርሃንን መታሰር በመቃወም ከፖሊስ ጋር ግጭት ውስጥ የገቡ ወጣቶች መኖራቸውን ያረጋገጡት ከንቲባው፤ ጥያቄ ያላቸው አካላት በተገቢው መንገድ ጥያቄያቸውን ማቅረብ ይችላሉ ብለዋል። ለአራት ተከታታይ ወራት ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት በማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰናል ያሉ ሲሆን፤ የደብረታቦር ኢየሱስ ቤተክርስትያን አካባቢ የተመረጠውም ለማሰራጫ አመቺና ከፍታ ያለው ስፍራ በመሆኑ ነው ተብሏል።

የደቡብ ጎንደር ሀገር ስብከት ስራ አስኪያጅ የሆኑት ሊቀ ኅሩያን ዮሐንስ መዝገቡ በበኩላቸው፤ የመንግስት አካላት ያቀረቡትን የማሰራጫ አንቴና ተከላ ተከትሎ ተደጋጋሚ ውይይትና ስብሰባ መደረጉን አስታውሰው፤ ቀድሞ የተጠየቀው ቦታ ከቤተክርስቲያኗ ጥቅምና አገልግሎት ጋር የሚጋጭ በመሆኑ እንዲቀየር ከመደረጉም ባለፈ በቅድመ ሁኔታ የግንባታ ፈቃዱ እንደተወሰነ ይናገራሉ። በዚህም የግንባታ ቦታው ታቦት የሚወጣበትን አቅጣጫ እንደማይነካ ተግባብተን ነበር ያሉ ሲሆን፤ አሁን ግጭቱ የተነሳው በዚህ ቦታ ላይ ቁፋሮ እየተካሄደ ነው የሚሉ ወጣቶች ጥያቄ በማንሳታቸው ሳይሆን እንደማይቀር መስማታቸውን ተናግረዋል።

አሁንም ቢሆን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተወያይተን ያለውን ችግር ለመፍታት ዝግጁ ነን ያሉት የደብረታቦር ከንቲባ አቶ ታደሰ፤ ከዚህ ውጪ በሆነ አካሄድ የሚመጣ አካል ካለ ግን እርምጃ ይወሰድበታል ብለዋል። አምስት የመኢአድ ፓርቲ አባላት መታሰርን በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄ ከንቲባው ሲመልሱ፤ “እስካሁን በቦታው የተለየ ቅስቀሳ አድርገዋል የተባሉ ሰዎች መያዛቸውን አውቃለሁ። የመኢአድ አባል ይሁኑ አይሁኑ ግን የምናውቀው ነገር የለም” ሲሉ መልስ ሰጥተውናል። የደብሩ አገልጋይ ናቸው የተባሉት አባ ብርሃኑን በተመለከተም ህዝብን በሚያጫርስ፣ ስርዓቱን በሚያፈርስ መልኩ ሰይፍና ጩቤ ይዛችሁ ውጡ በማለት ቅስቀሳ ማድረጋቸውን ተከትሎ በወረዳው ፖሊስ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

በደብረታቦር ኢየሱስ ቤተክርስትያን አካባቢ ይሠራል ተብሎ የሚጠበቀውን የቴሌቭዥን ማሰራጫ ተከትሎ በተነሳው ውዝግብ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የደብሩ አስተዳዳሪ መላከ ታቦር ኃ/ኢየሱስ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *