የቁጥር ዕውቀቴ ካናካቴው ከዳኝ! (ይሄይስ አእምሮ፣ ከአዲስ አበባ)

ስለምንም ነገር መጻፍ አልፈለግሁም ነበር፡፡ “ተጻፈ፣ ተጻፈ ግን እንዳልተጻፈ ሆነ” በማለት ወዳማርኛ ሲመለስ “ጮህን፣ ጮህን እንዳልጮህንም ሆን” ወይም በመገኛ ቋንቋው “ነባይነ፣ ነባይነ ከእምዘባይነ ኮነ” ተብሎ የተነገረውን ነባር ብሂል ልኮርጅና መጻፍ ብቻውን ትርፉ ድካም ብቻ መሆኑን በእግረ መንገድ ልጠቁም፡፡ የዚህች ሀገር ነገር እየፈጩ ጥሬ ወይንም አድሮ ቃሪያ እየሆነ መሄዱ በአርምሞ መቀመጥን ብቻ ከጋበዘ እሰዬው ነው፡፡ ከዚያ ባለፈ ይልቅ ጨርቃቸውን የሚጥሉና ራሳቸውን የሚያጠፉ ዜጎች ከእስከዛሬው በባሰ ቁጥራቸው እየጨመረ እንዳይሄድ እሰጋለሁ፡፡ መኖር ትርጉም ሲያጣ፣ ሀገር ባለቤት አልባ እየሆነች ማንም ሥርዓት አልባ ሲፈነጭባት፣ ለአመርቂ ሥራ ሳይሆን ነገርን ለማበለሻሸት ብልጣ ብልጡ ወደ ሥልጣን እየወጣ ሞኛሞኙ ግን ወደ ጓዳ ሲሰበሰብ፣ በ “ኳስ አበደች” ምትክ “ሀገር አበደች” ሲባልና ሁሉም ተያይዞ አቅል ሲያጣ… በዚህን ጊዜ ያልታበደ መቼ ሊታበድ? በዚህን ጊዜ ሞትን ያልተመኙ መቼ ሊመኙት? ሁሉም ነገር የግርምቢጥ ሆኖ ጉዳችን እየተንተከተከላችሁ ነው፡፡ ….

“የጥናትና ምርምር” ውጤቴን ልንገርህ ይልቁንስ፡፡ የቁጥር ዕውቀቴ ሙልጭ ብሎ ከቅንጭላቴ ወጣና ዐረፈው፡፡ ዱሮ ቁጥር አውቅ ነበር፡፡ ደመወዜ 500 ብር ሳለ ቁጥር በደምብ ይገባኝ ነበር፡፡ ጤፍ በኩንታል 30 ብር ሲሸጥ ቁጥር በሚገባ አውቅ ነበር፡፡ ያኔ በደጉ ዘመን በስሙኒና በሃምሳ ሣንቲም ክትፎ ስንበላ ቁጥር አውቅ ነበር፡፡ በዚያ ‹ክፉ› የኃይለ ሥላሤ ዘመነ መንግሥት የማዘጋጃ ቤት ሕንፃ በሦስት ሚሊዮን ብር ተጠናቀቀ ሲባል፣ ጥቁር አንበሣ ሆስፒታል በሦስት ሚሊዮን ብር ተሠራ ሲባል፣ የአቶ ገመቹ ደስታ ሐጎስ የመኖሪያ ቤት – ቪላ – በሁለት ሽህ የኢትዮጵያ ብር ተገንብቶ አለቀ ሲባል፣ አሥራ አንድ ጥርስ በወርቅ አርቲፊሺያል ጥርስ ለመተካት 90 ብር ወሰደ ሲባል… ያኔ በጅሎቹ ዘመን ቁጥር ይገባኝ ነበር፡፡ አሁንስ?

ነገር የቀሰቀሰብኝ እኮ ይሄ ዘሀበሻ የሚባል ድረገፅ ነው እናንተዬ! ምናለ ባልከፍተው ኖሮ? ዘሀበሻ “……ከዚህም ሌላ ፕሬዝደንት ኢሳያስ በባህርዳር ቆይታቸው፣ ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ጋር በመሆን ባህርዳር ዩንቨርስቲ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ ያስገነባውን  ግዙፍ ሆስፒታል እንደሚመርቁ ተሰምቷል” አይልልህ መሰለህ? ለነገሩ ዘሀበሾች ምን ያድርጉ የሰሙትን ነው የዘገቡት፡፡ (አፅንዖት  ከራሴ)

ይሄ ቢሊዮን የሚባል ነገር እንዲህ መቀለጃ ሆነ ማለት ነው? የሚሊዮኑ ነገር ቀርቶ ቢሊዮንም እንዲህ ዚቅ ይሠራበት? ሁለት ቢሊዮን ለመሆኑ ስንት ነው? በሀገራችን ምን እየተካሄደ ነው? በቀደም ለት ጠ/ሚ ዐቢይ መረቁት የተባለው መስኖ ፈጀ የተባለው 3.8 ቢሊዮን ነው፡፡ ያ ገርሞኝ ሳያበቃ አንድ ሆስፒታል ይህን ያህል ፈጀ መባሉ ከማስገረም እልፎ ያስደነግጣል፤ ዜግነቴ ትርጉም ቢኖረው ኖሮ ደግሞ የማስቆጨትን ድንበር አልፎ ያስቆጣል፡፡ በዚህ አጋጣሚ  የቁጥር ዕውቀቴን ማጣት ብገልጽ የሚቀየመኝ ያለ አይመስለኝም፡፡ እንዲያው ለነገሩ ያን ያህል ገንዘብ የፈጀ መስኖ ስንት ሄክታር አልምቶ ስንት ኩንታል እህል በስንተዜ ያመርት ይሆን? የወጣበትን ገንዘብ የሚመልስ በረከት ይኖረው ይሆን? እንጃ!

በየሚዲያው የምትሰሙት ቁጥር ያስበረግጋችኋል፡፡ ሰዎች በተለይም ፖለቲከኞችና በልማት ተብዬው መስክ የተሰማሩ የመንግሥት ሰዎችም የቁጥር ዕውቀታቸው እንደኔው ሳይከዳቸው የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ሦስት ወር ለማታገለግል ሚጢጢዬ ድልድይ 50 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጋቸውን በኩራት ሲገልጹ ብታዩ ስለነሱ ማፈሩ ራሱ ይከዳችሁና የምፀት ሳቃችሁን ትለቁታላችሁ – እንደማሽላዋ፡፡ ሳይመረቅ ለሚገማመስ የአሥር ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድ አንድ ቢሊዮን ሁለት መቶ አሥራ አንድ ብር ከዜሮ ዘጠና ሰባት ሣንቲም መውጣቱ ሲነገራችሁ ያላችሁ አማራጭ ጆሯችሁን መሸፈን ብቻ ነው፡፡ አንዲት በመዝገብ ላይ ብቻ ያለች መኪና ለማስጠገን፣ አንዲት የጤና ጣቢያ ለመገንባት፣ አንድ አነስተኛ ትምህርት ቤት ለመሥራት፣ አንድ ቤተ ክርስቲያን ለማነፅ፣ አንድ ፖሊስ ጣቢያ ለማቆም፣ አንድ መለስተኛ ጥናት ለማስጠናት፣ አንዲት የመስክ ሥራ ለማከናወን፣ አንድ አዲስ ንብረት ለመግዛት ወይም አሮጌ ዕቃ ለማስወገድ፣  ስንቱን ጠቅሼው…. በነዚህና እነዚህን በመሰሉ ሰበብ አስባቦች የሚዘረፈው የሀገር ሀብት አንድ አይደለም አሥር ኢትዮጵያዎችን በማሌዥያና ሲንጋፖር ደረጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንብቶ እነሆ ይል ነበር፡፡ ሀገርና ሕዝብ መጫወቻ ሆነዋል፡፡ የሀገር ካዝና በቀን ጅቦች ቁጥጥር ውስጥ ገብቶ ማንም እንደፈለገው እየዛቀ በልማትና በአገልግሎት ስም እየመዘበረው ነው – የቀን ጅቦች ስል ወያኔዎችን ብቻ ማለቴ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፤ ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የቀን ጅብ ሞልቷል፡፡ ሲመዘብሩ ደግሞ በሚሊዮኖችና ቢሊዮኖች እንጂ እንደዱሮው በይሉኝታ ገመድ ታስረው በመቶዎችና በሽዎች አይደለም፡፡ በሃይማኖት ያልለዘበ ስብዕና፣ በሞራል ያልተገነባ ሰውነት፣ በባህልና በሥርዓት ያልታሸ ዜጋ፣ ይሉኝታንና ሀፍረትን ሸጦ የበላ ትውልድ ሀገሪቱን ወርሮ በጥሎ ማለፍ የትግል ሥልት እየቦተረፋት ይገኛል – ቤትና ንብረት በአጭር ጊዜ የማፍራት ውድድሩ ደግሞ አይነሳ! ዛሬ ቪትዝ ይዞ የምታየው ወሮበላ ጓደኛውን ለመብለጥ ነገ ሀመር ይዞ ታየዋለህ፡፡ አውሮፓ ላይ የምትደነግጥበት መኪና እዚህ ባሉ ደናቁርት ሀብታሞች እንደሸሚዝ የሚቀያይሩት ነው፡፡ ማን ምን ይነግዳል? ስንት ያተርፋል? ስንትስ ማትረፍ አለበት? ማን እንዴት ከበረ? የሚንፈላሰስበትን ገንዘብ ከየት አመጣው? በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዴት እንዲህ ሊከብር ቻለ? ኑሮና ደመወዙ ይመጣጠናሉ ወይ? …. ብሎ የሚጠይቅ በሀገራችን የለም፤ ህግና ሥርዓት በሚከበሩበት የሠለጠነው ዓለም ውስጥ ግን አምስት ሣንቲም አላግባብ አትወጣም – አትገባም፡፡ ምክንያቱም ንቅዘቱና ሙስናው የማያንኳኳው ቤት የለምና፡፡ አለቃ ገ/ሃና “እዚያም ቤት እሳት አለ” እንዳሉት መሆኑ ነው፡፡ ባለ አሥር ሽህ ብር ደሞዝተኛው እኔ ወርን ከወር ለመግጠም ስንትና ስንት ብድር እየገባሁ ባለአምስት ሽህ  ደሞዝተኛው አቶ ግደይ ለቅምጡ አቶዝ ሲገዛ አያፍርም፤ እንዲያፍር የሚያደርገው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሥርዓትም የለም፡፡ እዚህች ሀገር ውስጥ እንዴት ይኖራል ታዲያ? የምትገርም ኢትዮጵያ ውስጥ ነን፡፡Read more

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *