የመከላከያ ሰራዊት በአዲስ መልክ ሊደራጅ ነው ተባለ

የኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 55ኛ መደበኛ ስብሰባ የመከላከያ ሰራዊትን በአዲስ መልክ የሚያደራጅ ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅ ላይ ውሳኔ ማስተላለፉን መንግስታዊው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘገበ። ምክር ቤቱ በሌሎች ሶስት ጉዳዮች ላይም ውሳኔ አሳልፏል ተብሏል።ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ የመከላከያ ሰራዊት አዋጅን ለማሻሻል የሚያስችል የህግ ረቂቅ እንደሆነ የዜና ወኪሉ ዘግቧል። በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ለውጥ ተከትሎ መከላከያ ሰራዊቱ አገራዊ ተልዕኮውን በተሻለ ብቃት እንዲወጣ፣ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የሪፎርም ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የጠቀሰው ምክር ቤቱ የሰራዊቱን የግዳጅ አፈጻጸም ብቃት ለማጠናከርም የህግ ማዕቀፍ አስፈላጊ መሆኑን አመልክቷል።

በመሆኑም ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ ማሻሻያዎችን በማከል ረቂቅ አዋጁ እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩ ተገልጻል።ምክር ቤቱ በዛሬው ስብሰባው የቀረቡለትን የሁለት የመንግስት መስሪያ ቤቶች መተዳደሪያ ደንቦችን ተመልክቶም ውሳኔ አሳልፏል። ስልጣንና ተግባራቸውን ለመወሰን ረቂቅ ደንብ የተዘጋጀላቸው መስሪያ ቤቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን እና የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ናቸው። ምክር ቤቱ የፌዴራል ዓቃቢያን ህግ የመተዳደሪያ ረቂቅ ደንብ ላይም ተወያይቶ ደንቡ ስራ ላይ እንዲውል መወሰኑን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

Mereja.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *