የግብጹ ባለስልጣን የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በሚቀጥሉት አመታት እንደሚፈርስ ተናገሩ

የግብፅ የውሃ ሀብት ምርምር ማእከል የቀድሞ ሃላፊና የአለም አቀፍ ግድቦች ኤክስፐርት የሆኑት አህመድ አል ሸናዊ ለግብፁ አል ማስሪ አል ዩም ጋዜጣ በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በሚቀጥሉት አመታት እንደሚፈርስ ተናገሩ፡፡ በአረብኛ ቋንቋ የሰጡትን መግለጫ ኢጂፕት ኢንዲፔንደንት ጋዜጣ ወደእንግሊዘኛ ተርጉሞ ዛሬ ለንባብ አብቅቶታል፡፡ እንደጋዜጣው ምሁሩ ስለግድቡ በሰጡት ትንበያ ግድቡ የተሰራው በተሰነጣጠቀ መሬት ላይ እንደሆነ ጠቅሰው ይህ ማለት ደግሞ አካባቢው ለመሬት መንቀጥቀጥ የተጋለጠ መሆኑን እንደሚያሳይ አስረድተዋል፡፡ ከእነዚህ መንቀጥቀጦች አንዱ ግድቡን እንደሚያፈራርሰውም ነው የተናገሩት፡፡የግድቡ የተወሰነ ክፍል ባለፉት አመታት ለሁለት ጊዜ ፈርሶ እንደነበር የተናገሩት ሸናዊ ‹‹ይህ በራሱ ግድቡ እድሜው አጭር እንደሆነና ከበድ ያለ መሬት መንቀጥቀጥ ሲያጋጥመው ሙሉ በሙሉ እንደሚፈርስ አመላካች ነው›› ብለዋል፡፡ መግለጫቸውን በመቀጠል ከጥቂት ወራት በፊት ሱዳንን ያጥለቀለቀውና በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት የዳረገው ጎርፍ ከዚሁ ከግድቡ የወጣ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በአካባቢው የደረሰው መሬት መንቀጥቀጥ የግድቡን በሮች በመሰነጣጠቁ በ15 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ሱዳን ውሃ በጎርፍ መልክ ሊሄድ መቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ጎርፉ መደበኛ ጎርፍ ሳይሆን ከግድቡ መሰንጠቅ ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ነበር›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ጨምረውም ‹‹የሕዳሴው ግድብ 145 ሜትር ርዝመት ስላለው በርካታ ውሃ ማጠራቀም ይችላል፡፡ ስለዚህ ከፈረሰ ጉዳቱ በጣም ከባድ ነው የሚሆነው፡፡ ግዶቦች ብዙውን ጊዜ አጠር ተደርገው የሚሰሩት ለዚህ ነው፡፡›› ብለዋል፡፡
በመግለጫቸው ማጠቃለያም ይህ ግድብ የሚፈርስ በመሆኑ ግብፅ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ አቤት ማለት እንደሚኖርባት ምክር ለግሰዋል፡፡ ግድቡ በሚፈርስበት ወቅት ዋነኛ ተጎጂዎቹ ግብፅና ሱዳን በመሆናቸው ከወዲሁ በኢትዮጵያ ላይ ክስ በመመስረት ችግሩ ከመምጣቱ በፊት ማስቆም ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *