የዴር ሱልጣን ነገር

 

ሙዐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት

የእሥራኤል መንግሥት የፈረሰውን የዴር ሡልጣን የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ለመጠገን ሲነሡ ግብጻች በከፍተኛ ሁኔታ እየተቃወሙት ነው፡፡ በአንድ በኩል በኢየሩሳሌም ያሉ መነኩሴዎቻቸው ያለ የሌለ ኃይል በመጠቀም በሩን ይዘጋሉ፡፡ የኢየሩሳሌሙ ጳጳሳቸው እንኳን አልቀሩም በኃይል በር ለመዝጋት ሲታገሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የአካባቢውን ዐረቦች ለመቀስቀስ ይሞክራሉ፡፡ የኮፕቲክ ሲኖዶስም በፓትርያርኩ በኩል መግለጫ አውጥቷል፡፡ የግብጽ መንግሥትም ጫና እንዲያደርግ እየወተወቱት ነው፡፡ የመካከለኛው ምሥራቅ ሚዲያዎች ዘገባቸው ሁሉ ለግብጽ የሚያደላ ነው፡፡

ግብጾቹ አጋጣሚውን በመጠቀም ገዳሙን ማስዘጋትና መውረስ ነው ዕቅዳቸው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በአስቸኳይ አምስት ነገሮችን ማድረግ አለበት፡፡

1.አስቸኳይ መግለጫ በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛና በዐረብኛ ቋንቋዎች በማውጣት ለየሚዲያው ማሳወቅ፤ በዚህ መግለጫው ዴር ሡልጣን የኢትዮጵያ የማይናወጽ ርስቷ መሆኑን በማስረጃ ማሳየትና ለመላው ዓለም ኢትዮጵያውያንና አፍሪካውያን ጥሪ ማድረግ

2.የኢትዮጵያ መንግሥት በዲፕሎማሲው መሥመር አስፈላጊውን እንዲያደርግ መጎትጎት

3.የእሥራኤልን አምባሳደር በአስቸኳይ ጠርቶ ማነጋገር

4.ግብጻውያን ከዚህ አፍራሽ ተግባራቸው ካላቆሙ ግንኙነታችን ሊበላሽ እንደሚችል ቆራጥ አቋም የሚያሳይ ደብዳቤ ለኮፕቲክ ሲኖዶስ መላክ

5.በኢትዮጵያ ከሚገኙ የእምነት ተቋማት ጋር በመነጋገር የጋራ አቋም መያዝ

በየዓለማቱ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን
1. በእሥራኤል ኤምባሲ ፊት ሰልፍ በማድረግ
2. የምንችል ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ
3. በየአለንበት ድምጻችንን በማሰማት
4. ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾችን በጉዳዩ ዙሪያ አስረድቶ በማሰለፍ የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ጊዜው ዛሬ ነው፡፡

ከዚሁ ጋር ለዘለቄታውም ቢሆን ከሊቃነ ጳጳሳት፣ ከሊቃውንት፣ ከታወቁ ዲፕሎማቶች፣ ከታዋቂ ሰዎች፣ ከጋዜጠኞች፣ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተወጣጣ ‹የዴር ሡልጣን ጉዳይ ብሔራዊ ኮሚቴ› ተቋቁሞ የዴር ሡልጣን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ችግር በዘላቂ ሁኔታ የሚፈታበትን አቅጣጫ ይዞ ይሥራ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አቶ ሥዩም መስፍንና ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኃኖም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እያሉ ቅዱስ ሲኖዶስን ደጋግመው ለማሳሰብ ሞክረው ነበር፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ለኢትዮጵያ መንግሥት ከጻፈ ብሔራዊ ኮሚቴ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲቋቋምም ሐሳብ አቅርበው ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ለዘላቂው የሚያዋጣን እርሱ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *