የጫልቱ ታከለ ፈተና እና ፅናት

ጸሐፊ፡- ማሕሌት ፋንታሁን

ከአንዴም ሁለት ጊዜ የእስርን ሕይወት ተጋፍጣለች፡፡ በማዕከላዊ እና የትነቱ በማይታወቅ የእስር ቦታ የማሰቃየት ተግባር ተመሥርቶባታል፡፡ ከ8 ዓመታት በላይ ከዕድሜዋ ላይ ተቆጦ በእስር ባክኗል፡፡ ጫልቱ ታከለ፡፡ እርሷ ግን በፅናት ፈተናዋን ተወጥታለች፡፡ በእስር ቤት ውስጥ ከአስቸጋሪ ሁኔታዎች እና ክልከላዎች ጋር እየታገለች የመጀመሪያ ዲግሪዋን እስከመያዝ ደርሳለች፡፡ በዚህ ትረካ የጫልቱ ታከለን ያለፉት ዐሥር ዓመታት ጉዞ በወፍ በረር እንቃኛለን፡፡

ጫልቱ ታከለ ማን ናት?

ጫልቱ ታከለ በኦሮሚያ ክልል ሻምቡ ከተማ ነው እድገቷ። የ34 ዓመት ወጣት ስትሆን ሁለት ጊዜ የኦነግ  አባል ነሽ ተብላ ታስራ በአጠቃላይ ለዘጠኝ ዓመታት በእስር አሳልፋለች። በኦሮሞ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ግፍ እና ሰቆቃ ስታይ በማደጓ እንዲሁም ብዙ የምታውቃቸውን ሰዎች በኢሕአዴግ ስርዓት ማጣቷ ኢሕዴግን ለመቃወም ምክንያት እንደሆናት ነገር ግን ስርዓቱን በግሏ ከመቃወም ውጪ ከኦነግ ጋርም ሆነ ሌላ ድርጅት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳልነበራት የምትናገረው ጫልቱ፣ መጀመሪያ የታሰረችው በግንቦት ወር 2000 ሲሆን በወቅቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ ሁለተኛ ዓመት ተማሪ ነበረች። በቀረበባት ክስ የ12 ዓመት ፍርድ ከተፈረደባት በኋላ በአመክሮ ስምንት ዓመት ከታሰረች በኋላ ሰኔ 18/2008 ቀን ተፈታች።  “ቃሊቲ ከገባሁ እና ከተፈረደብኝ በኋላ የደኅንነት ሰዎች መጥተው አናግረውኝ በስህተት እንዳሰሩኝ እና ጥፋተኛ ነኝ ብዬ ይቅርታ ብጠይቅ እንደሚፈቱኝ ሲጠይቁኝ ‘ጥፋተኛ አይደለሁም፤ ይቅርታም አልጠይቅም’ አልኳቸው”  የምትለው ጫልቱ በቃሊቲ ቆይታዋ በርቀት ትምህርት ከሶስዮሎጂ ዲፓርትመንት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ጨርሳለች።

ከተፈታች በኋላ በተማረችው ትምህርት ሥራ ለማግኘት የተለያየ ቦታ ብታመለክትም አሰሪዎች እሷን በመቅጠራቸው የሚደርስብን ቅጣት ይኖራል በሚል ስጋት ዕድሉን ሊሰጧት ስላልቻሉ ወደ ሱዳን ሔዳ ሥራ ለመሥራት ትወስናለች። ከተፈታች ከስምንት ወር በኋላ ለሥራ ወደ ሱዳን ለመሔድ ከአዲስ አበባ ተነስታ ወደ ጎንደር መንገድ ላይ እያለች እንጦጦ ኬላ ላይ በፖሊስ ተይዛ ኦነግን ለመቀላቀል ልትሔጂ ነበር ተብላ የካቲት 30/2009 ቀን በድጋሚ ታስራለች። ከአምስት ወር በላይ በፌደራል የወንጀል ምርመራ ማዕከል (‹ማዕከላዊ›) ከቆየች በኋላ የሽብር ክስ ተመሥርቶባትም ክሷን በእስር ሆና እየተከታተለች እያለ ከ11 ወር የእስር ቆይታ በኋላ መንግሥት “ለሕዝብ እና ለመንግሥት ጥቅም ሲባል” የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ የሚል ውሳኔ ባስተላለፈበት ጊዜ  የሷም ክስ ተቋርጦ ተፈታለች።

እርቃን ሆኖ ስቃይ

ጫልቱ ታከለ የእስር ፈተናን በድል ያሸነፈች ጀግና ናት፤ በመጀመሪያው እስሯ ከአስተዳደራዊ ክልከላዎች ጋር ተጋፍጣ የመጀመሪያ ድግሪዋን ሠርታለች፡፡

ግንቦት 2/2000 ቀን ነበር መጀመሪያ ጊዜ የታሰረችው። የምትኖርበት ቤት መጥተው የወሰዷት ፖሊሶች የእስር ማዘዣም ሆነ የቤት ብርበራ ፈቃድ አልያዙም ነበር። ጫልቱ ስለአያያዟ ሁኔታ እና የማእከላዊ ቆይታዋ ስትናገር “የምኖርበት ቤት ፖሊሶች ሲመጡ እኔን ፈልገው ይሆናል ብዬ በፍፁም አልጠረጠርኩም። የአክስቴን ልጅ፣ የወንድሜን ሚስት፣ የቤት ዘበኛ እና እኔን ነበር ወደ ማዕከላዊ የወሰዱን። ማዕከላዊ ስንደርስ የወንድሜን ሚስት ሌሎች ሴት እስረኞች ያሉበት ክፍል ሲያስገቧት እኔን ግን ከሌሎች ሴት እስረኞች ለይተው ለብቻዬ አንድ ክፍል ውስጥ አስቀመጡኝ። ቀን፣ ማታ እና ለሊት ለምርመራ እያሉ ይጠሩኛል። የምመረመርበት ክፍል ውስጥ በአንድ ጊዜ ሰባት ስምንት እና ከዛ በላይ መርማሪዎች ይኖራሉ።

“ልብሴን አውልቄ እራቁቴን እንድቆም ካደረጉ በኋላ እጄን በካቴና አስረው ሰቅለውኝ ይገርፉኛል። በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ አብረውኝ ይማሩ የነበሩ አምስት ተማሪዎች ከደኅንነት አካላት ይደርስባቸው በነበረ ክትትል ብዛት እና ስጋት ጠፍተው ነበረ። በወቅቱ ደግሞ ቦሌ እና ኢምፔሪያል ኖክ ማደያዎች ላይ ቦንብ ተወርውሮ ስለነበረ፤ ከጠፉት ተማሪዎች ውስጥ አንዱ የኔ ጓደኛ በመሆኑ ‹ከሱ ተልእኮ ተቀብዬ ኢምፔሪያል ሆቴል ያለ ኖክ ማደያ ላይ ቦንብ ጥያለው፤ እንዲሁም ከኦነግ ጋር ግንኙነት አለኝ› ብዬ ቃል እንድሰጥ ነበር መርማሪዎቹ የሚደበድቡኝ። በዚህ መልኩ ለአምስት ቀናት በማዕከላዊ ከቆየሁ በኋላ አመሻሽ ላይ እቃሽን አዘጋጂ ተባልኩ። እኔም ከሌሎች ሴት እስረኞች ክፍል ሊቀላቅሉኝ ነው ብዬ አስቤ ነበረ።” ትላለች፡፡ ይሁን እንጂ ያሰበችው አልሆነም፡፡

ድብቁ “የምርመራ ቦታ”

– አራት ወር ሙሉ ፍርድ ቤት አለመቅረብ

– ኢሰብኣዊ ማሰቃየትRead more>>

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *