ኢሳትና የብሄር ፖለቲካው ጦርነት

ኢሳትና የብሄር ፖለቲካው ጦርነት |

የአማራ ብሄርተኞችና ኢሳት

ኢሳትና የብሄር ፖለቲከኞች ሊጣጣሙ አልቻሉም፡፡ ይህ ውዝግብ እየጦዘ ሄዶ በስተመጨረሻ ከሰሞኑ በጣቢያውና በኦሮሞ ፖለቲኞች መካከል ሲፈነዳ ታይቷል፡፡ ሁኔታው ድንገት የተከሰተ ሳይሆን ከመሰረታዊ የአቋም ልዩነቶች ጭምር የመነጨ መሆኑን ከሌሎች ብሄር ተኮር አደረጃጀቶችም ጭምር ጋር በማያያዝ እንመለከታለን፡፡

የአማራ ብሄርተኞች በኢሳት ላይ ሰፊ ዘመቻን ከከፈቱ ሰነባብተዋል፡፡ አንዳንዶቹ በተለያዩ ሚዲያዎች ጣቢያውን “ፀረ አማራ” በማለት በግልፅ የፍርጃ ዘመቻን ሲከፍቱ ታይተዋል፡፡ ሁኔታው በሚገባ ሲመረመር አክቲቭስቶቹ በሚዲያው ላይ የከፈቱት ዘመቻ ያዝ ለቀቅ የሚታይበት ሳይሆን እጅግ የተቀናጀና ተከታታይነት ያለው ነበር፡፡

በእነዚህ የሚዲያው ተቃዋሚዎች ከሚነሱት መሰረታዊ የተቃውሞ ቅሬታዎች መካከል፤ “ጣቢያው ስለአማራ ሰቆቃ አይዘግብም፣ ቢዘግብም አቀራረቡ አሉታዊ በሆነ መልኩ ነው፣ ፀረ አማራ ኃይሎችን መድረክ እየሰጠ የአማራ ብሄርተኝነትን ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ለመቸለስ ተግቶ ይሰራል” የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ሌላኛው ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚችለው ጭብጥ፤ ጣቢያ የግንቦት ሰባት ልሳን የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ በአማራ ብሄርተኛ ኃይሎችና በአርበኞች ግንቦት ሰባት መካከል ከባድ የሆነ የሀሳብ ፍለሚያ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡

የአማራ ብሄርተኞች “ አማራ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ሲታገል ላላፉት ሁለት አስርት ዓመታት ህዝቡ ላይ እስከ ዘር ማጥፋት የዘለቀ የተቀነባበረ ጥቃት የደረሰበት በኢትዮጵያዊነቱ ሳይሆን በአማራነቱ ነው” በማለት የአማራ ህዝብ ብሄርተኝነቱን አጠናክሮ ራሱን በአማራነት በማደራጀት ህልውናውን ማስጠበቅ ያለበት መሆኑን አጥብቀው ይከራከራሉ፡፡

አማራው ካለፈበት ሰፊ የሀገር ምስረታ (Nation building) ሥነ ልቦና እና ታሪካዊ ሂደት አኳያ በኢትዮጵያ አንድነት ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ ብሄር ዘለል ፓርቲዎችን የማስተናገድ መደላድልም ያለው መሆኑ እሙን ነው፡፡ ከእዚህ ብሄር ዘለል ህብረ ብሄራዊ ፓርቲዎች መካከል የሚጠቀሰው ደግሞ ግንቦት ሰባት ነው፡፡

ይህ ሁኔታ በተለይ “ከዚህ በኋላ አማራ በኢትዮጵያ አንድነት ስም መስዋዕትነት መክፈል የለበትም” የሚል የፀና አቋም ላላቸው የአማራ ብሄርተኛ አቀንቃኞች ፈፅሞ የማይዋጥ ሆኖ ታይቷል፡፡

ግንቦት ሰባትም ቢሆን ወደ ሀገር ውስጥ ከገባ በኋላ ከአዲስ አበባው አቀባበል ቀጥሎ ተከታታይ ስብሰባዎችን እና ውይይቶችን ያካሄደው በአማራ ክልል ከተሞች ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በአማራ ብሄርተኞችና በግንቦት ሰባት የአንድነት ኃይሎች መካከል የነበረውን የከረረ ልዩነት የበለጠ አጡዞታል፡፡

ኢሳት “ለኢትዮጵያ የብሄር ፖለቲካ አይጠቅምም” በማለት በግልፅ ያወግዛል፡፡ አሁን ያለው የብሄር ፌደራሊዝም አወቃቀርም እንዲቀየር አጥብቆ የሚሰራ መሆኑንም በተደጋጋሚ ይናገራል፡፡

ይህ አቋሙ ከብሄርተኞች ጋር ሰፊ የሚዲያ ጦርነት ውስጥ ከቶታል፡፡ በተለይ ለግንቦት ሰባት ከሚሰጠው የሚዲያ ሽፋን ጋር በተያያዘ በአማራ ብሄርተኞች በኩል ዘመቻ እንዲከፈትበት አድርጓል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ በአዲሱ የአማራ ብሄርተኛ አቀንቃኞችና እንደ ግንቦት ሰባት ባሉት የአንድነት ኃይሎች መካከል ያለው የትግል ፍትጊያ “የብሄር ፖለቲካ ለኢትዮጵያ አይጠቅምም የሚል የፀና አቋም ላለው ኢሳት በሚዲያው ጦርነት ውስጥ ፍልሚያ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፡፡Read more>>>

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *