ተድበስብሶ የቀረው የቂሊንጦ ቃጠሎ ጉዳይ (ማሕሌት ፋንታሁን)

ተድበስብሶ የቀረው የቂሊንጦ ቃጠሎ ጉዳይ

የአግ7፣ ኦነግ እና አልሻባብ አባል በመሆን እና ተልእኮ በመቀበል ለቂሊንጦ ማረሚያቤት ቃጠሎ፣ ለሰው እና ንብረት መጥፋት ተጠያቂ ናችሁ ተብለው በሽብር ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩ 38 እስረኞች እንደነበሩ የሚታወስ ነው።

ሚያዚያ 30/2010 በተሰጠው ብይንም 8 ተከሳሾች በነፃ ተሰናብተዋል። 26ት ተከሳሾች ደግሞ አንቀፅ ተቀይሮ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 464 (2)ሀ [1ኛ፣ 4ኛ፣ እና 15ኛ ተከሳሾች] ፣ አንቀፅ 464(1)ሐ [14ኛ፣ 16ኛ፣ 19ኛ ፣ 20ኛ፣ 22ኛ እና 23ኛ ተከሳሾች] ፣ አንቀፅ 464(2) ለ [2ኛ፣ 3ኛ፣ 5ኛ፣ 8ኛ፣ 10ኛ፣ 12ኛ፣ 13ኛ፣ 17ኛ፣ 24ኛ፣ 26ኛ፣ 37ኛ እና 38ኛ ተከሳሾች] እንዲሁም አንቀፅ 464 (2) ለ እና 494 (2) [9ኛ፣ 25ኛ፣ 30ኛ፣ 35ኛ እና 36ኛ ተከሳሾች] እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል። ብይኑ ከተሰጠ በኋላ 26ቱ ተከሳሾች ክሳቸው የተቋረጠ ሲሆን የተቀሩት 4ት ተከሳሾች (31ኛ፣ 32ኛ፣ 33ኛ እና 34ኛ ተከሳሾች) ደግሞ የወንጀል ህጉን 464(2)ለ ን [የእስረኞች አመፅ መምራት እና የማደራጀት ወንጀል] እና 540 ን [የሰው መግደል ወንጀል] እንዲከላከሉ ተወስኗል።

የቂሊንጦ ቃጠሎ፣ የጠፋው የሰው ህይወት እና የንብረት ውድመት አራቱ ተከሳሾች ላይ ብቻ ተደፍድፏል። 31ኛ ተከሳሽ ጌታቸር እሸቴ፣ 32ኛ ተከሳሽ ቶፊቅ ሽኩር ፣ 33ኛ ተከሳሽ ሸምሱ ሰኢድ እና 34ኛ ተከሳሽ ፍፁም ጌታቸው ላይ። እነዚህ አራት ተከሳሾች ተከላከሉ ያስባላቸው እና የተጠቀሰባቸው የምስክሮች ቃል ላይ በተከሳሾቹ ተገለዋል ተብለው በስም የተጠቀሱት አራት እስረኞች ብቻ ናቸው። ማረሚያ ቤቱ ባመነው እንኳን 23 እስረኞች ሞተዋል። ትክክለኛው የሟቾች ቁጥር ደግሞ ከ75 በላይ እንደሆነ ነው የሚገመተው። ተከሳሾቹ ፈፀሙት አልፈፀሙትም ፍርድ ቤቱ የሚያየው ጉዳይ ሆኖ የተቀሩት የሞቱ እስረኞችስ ጉዳይ? የማረሚያ ቤት ሃላፊዎችን ሃጢያት በመደበቅ የሚታወቀው የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር የነበረው ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሄር መጋቢት 27 ቀን 2009 ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት የማረሚያ ቤቱ የጥበቃ አባላት ከውጪ ወደ ውስጥ ሲተኩሱ እንደነበር ገልፇል። የእሳት አደጋ መስሪያ ቤት በፃፈው ሪፖርትም የማረሚያ ቤቱ ወታደሮች ይተኩሱ ስለነበር ስራቸውን ለመስራት ተቸግረው እንደነበረ ገልፀዋል። ነገር ግን አንድም የተጠየቀ የማረሚያ ቤት ሃላፊም ሆነ ወታደር የለም። ታዲያ የቂሊንጦ ቃጠሎን፣ የጠፋውን ሰው ህይወት እና ንብረት በተመለከተ አራቱ ተከሳሾች ላይ ብቻ ደፍድፎ ሲተኩሱ ነበር የተባሉት የማረሚያ ቤቱ ወታደሮች/ሃላፊዎች ከተጠያቂነት ማሸሽ ምን ማለት ነው? ሟች እስረኞች በህይወት የመኖር መብታቸው ባይከበር ገዳዮቻቸው ለፍርድ መቅረብ አልነበረባቸውም?

አራቱ ተከሳሾች ነገ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መከላከያቸውን ማሰማት ለመጀመር ቀጠሮ አላቸው። መከታተል የምትፈልጉ ጠዋት 3 ሰአት ላይ 19ኛ ችሎት መምጣት ትችላላችሁ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *