ይድረስ ለግልገል ጨቋኞች፦ ነፃነትን ለማጣጣም በቅድሚያ ራስን ከጨቋኝ አመለካከት ነፃ ማውጣት!! [ስዩም ተሾመ]

ደርግ + ኢህአዴግ = 17 + 27 = 44 አመታት፡፡ በእነዚህ 44 አመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሽብር የተሞላ ነው፡፡ ደርግ ቀይ_ሽብር ሲለው ኢህአዴግ ደግሞ ፀረ_ሽብር ይለዋል፡፡ የደርግ መንግስት በዘመቻ፣ ኢህአዴግ ደግሞ በአዋጅ ዜጎችን ለሞት፥ እስራትና ስደት ዳርገዋል፡፡

በዚህ መልኩ ዜጎች ለመከራና እንግልት የተዳረጉበት መሠረታዊ ምክንያት የተለየ ፖለቲካ አቋምና አመለካከት መያዝ/መግለፃቸው ነው፡፡ የሁላችንም መብትና ነፃነት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ሰርዓት ለመዘርጋት የሚደረገው ጥረት የሚጀምረው የዜጎችን የሃሳብና አመለካከት ነፃነት ከማክበርና ማስከበር ነው!!

ትላንት ማታ በሚሊኒዬም አዳራሽ በቀረበው ዝግጅት ላይሃጫሉ_ሁንዴሳ የራሱን ሃሳብና አስተያየት በዘፈን መልክ አንጎራጉሯል! በተመሣሣይ ቴዲ_አፍሮ የራሱን ሃሳብና አስተያየት በንግግር መልክ ገልጿል፡፡ ሁለቱም አርቲስቶች የመኑበትን አቋምና አመለካከት በመግለፃቸው ምክንያት ለእስራትና እንግልት ተዳርገዋል፡፡ ላለፉት አመታት ቲዲም ሆነ ሃጫሉ በሀገራቸው በሰላም መኖርና መስራት አይችሉም፡፡

ያ… ክፉ ግዜ ማለፉን ለማብሰር ሁለቱም አርቲስቶች በዝግጅቱ ላይ በክብር ተጋብዘዋል፡፡ ሃጫሉ ያቀረበውን የዘፈን ስንኞች እየመዘዙ በኦሮሞ_በጎሰኝነት፣ የቴዲን ንግግር የመነዘሩ በኦሮሞ ጠላትነት መፈረጅ አግባብ አይደለም፡፡ ትላንት ሃጫሉ እና ቴዲ ለብዙ አመታት ዋጋ የከፈሉበትን የሃሳብና አመለካከት ነፃነት በተግባር አረጋግጠዋል!!

የሁለቱ አድናቂዎች ደግሞ በየፊናቸው ጎራ ለይተው ጅምላ ፍረጃ ጀምረዋል፡፡ ቴድ ሆነ ሃጫሉን ማድነቅ መብት ነው! ቴዲን ለማድነቅ ሃጫሉን ማጣጣል፣ ሃጫሉን ለማድነቅ ቴዲን ማጣጣል በአጉል ግብዝነት የተሞላ ኋላቀር አመለካከት ነው!! ቴዲ አፍሮ “የአፄ ሚኒሊክ አምላክ ይመስገን”፣ ሃጫሉ ደግሞ “አሁንም የኦሮሞ ህዝብ በግፍ እየተገደለ ነው” ማለቱን እንደ ወንጀል በመቁጠር የግለሰቦቹን ስብዕና በሚነካ መልኩ የስድብ ናዳ እና ዛቻ የሚያወርዱ ዛሬም የደርግና ኢህአዴግ አፋኝ የፖለቲካ አመለካከትን የሚያራምዱ ናቸው፡፡

 

ነፃነትን ለማጣጣም በቅድሚያ ራስን ከጨቋኞች አመለካከት ነፃ ማውጣት ያስፈልጋል!! “ሁሉም ነገር እኔ ባሰብኩት፥ በፈለኩትና ባቀድኩት መንገድ መሄድ አለበት” በሚል ጭፍን አቋምና አመለካከት እየተመሩ (እየተደናበሩ) የተለየ ሃሳብና አስተያየትን በጉልበት ለመጨፍለቅ መጣር የደርግና ኢህአዴግ ርዝራዥ መሆን ነው፡፡ እንዲህ ያለ አቋምና አመለካከት ያላቸው ልሂቃን እድልና አጋጣሚ ቢያገኙ የተለየ ሃሳብና አስተያየትን እንደ ወንጀል በመቁጠር በቀይ-ሽብር እና ፀረ-ሽብር ሀገርን ያምሳሉ!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *