በታራሚዎች ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊት የፈጸሙ ኃላፊዎችና ተባባሪዎቻቸው በሕግ ሊጠየቁ ነው

ሰሞኑን ከኃላፊነታቸው የተነሱ የማረሚያ ቤት ኃላፊዎችና ተባባሪዎቻቸው በፍርደኞችና የክስ ሒደታቸውን በመከታተል ላይ በነበሩ እስረኞች ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊት መፈጸማቸው በቀጣይ በሚደረግ ምርመራ ከተረጋገጠባቸው፣ በሕግ እንደሚጠየቁ ተገለጸ፡፡

ታራሚዎችና እስረኞች ከፍተኛ የሆነ በደልና ስቃይ እንደደረሰባቸው በቅርቡ ከእስር የተፈቱ ዜጎች እየገለጹ በመሆኑ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኃላፊዎችን በማንሳት አዳዲስ ኃላፊዎችን ሾሟል፡፡

የቀድሞ ኃላፊዎችን በማንሳት ተተኪ ኃላፊዎች መሾማቸውን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት ዓቃቤ ሕግ ብርሃኑ ፀጋዬ እንደተናገሩት፣ የማረሚያ ቤቶቹ አስተዳደር የተቋቋመበትን ዓላማ ከማሳካት አንፃር ከፍተኛ ክፍተት የሚታይበት ነው፡፡

‹‹ተቋሙ ግዴታውን ባለመወጣቱ ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር በተገናኘ ከፍተኛ ቅሬታ እየቀረበበት ነው፡፡ በማንም ይሁን በማን የተፈጸመ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ መጣስ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን መጣስ ደግሞ ወንጀል ነው፡፡ በማረሚያ ቤት ውስጥ ታራሚ በሆነ ዜጋ ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸም ደግሞ ከሕገ መንግሥቱ ጋር መጋጨት ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ጥሰዋል ተብለው በተከሰሱ ወገኖች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸም ወንጀል በመሆኑ፣ በወንጀሉ ውስጥ ገብተው የተገኙ ኃላፊዎችና ተባባሪዎቻቸው ላይ ማጣራት ተደርጎ ለሕግ እንደሚቀርቡ ዓቃቤ ሕጉ አስታውቀዋል፡፡

ዴሞክራሲያዊ አገር እየገነባን በመሆኑ ሕገ መንግሥቱ ሊከበር ይገባል ያሉት ዓቃቤ ሕጉ፣ በሕግ ቁጥጥር ሥር ያለን ዜጋ አርሞና አንፆ ማውጣትና ሕግ አክብሮ አምራች ኃይል እንዲሆን ማድረግ ሲገባ፣ አካልን አጉድሎና ሰብዓዊ ክብሩን ገፎ የሚያወጣ ተቋም መሆን የለበትም ብለዋል፡፡read full story

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *