የአልጀርስ ስምምነት፡ ባላንጣነትን የወለደው የ‹‹ሰላም ሰነድ››

የከፋ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጥፋትን ባስከተለው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ የድንበር ጦርነት ማግስት ሁለቱን ሀገራት ለእርቅና መግባባት እንደሚያበቃ ግምት የተሰጠው ሰነድ በአልጄሪያ ዋና ከተማ አልጀርስ ተፈረመ፡፡

ታህሳስ 3 ቀን 1993 በቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና የኤርትራው ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተፈረመው ባለ 6 አንቀጽ ሰነድ አራት መሰረታዊ ግቦች ነበሩት፡፡

እነርሱም፡-

• በሁለቱ ሀገራት መካካል ያለውን የባላንጣነት መንፈስ ማቆም፣ ሀገራቱ ከዛቻ እና የሃይል እርምጃ እንዲቆጠቡ ማድረግ፤

• ቀደም ብሎ በሰኔ 1/1992 የተደረሰውን በባለንጣነት ያለመተያየት ስምምነት እንዲከበር እና እንዲፈጸም ዋስትና መስጠት፤

• በእስር ያሉ የጦር ምርኮኞች እና ግለሰቦች ተለቀው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማስቻል፤

• ሁለቱ ሀገራት በግዛቶቻቸው ውስጥ ላሉ የሌላኛው ወገን ዜጎች ሰብአዊ እንክብካቤ እንዲያደርጉ ድልድልይ መሆን ናቸው፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ግቦች በየተራ ይሳኩ ዘንድ ሰነዱ ነጻ የድንበር እና የካሳ ኮሚሽኖች እንዲቋቋሙ መሰረት ሆኗል፡፡

5 አባላት ያሉት የኢትዮ ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን የራሱን ምርመራ አድርጎ፣ አለመግባባት የፈጠሩ የድንበር ቦታዎች ለየትኛው ሀገር እንደሚገቡ ለመወሰን እንዲችል በወቅቱ ከስምምነት ተደርሷል፡፡

በሰነዱ አንቀፅ አንቀጽ 2 (2) ቀደም ብለው የተገቡ የቅኝ ግዛት ህጎችን እና ዓለም አቀፍ ህግን ተመስርቶ ኮሚሽኑ ውሳኔውን እንደሚያስተላልፍ ተጠቅሷል፡፡

እንዲሁም በአንቀጽ 2 (15) ላይ ኮሚሽኑ የሚሰጠው የወሰን እና ማካለል ውሳኔ የመጨረሻ እና ገዢ እንደሚሆን ተዘርዝሮም ነበር፡፡

የአልጀርስ ስምምነት፡ ባላንጣነትን የወለደው የ‹‹ሰላም ሰነድ››

ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ማስረጃ በማቅረብ መቀመጫውን ኔዘርላንድ ዘሄግ ባደረገው ኮሚሽን ፊት ተከራክረዋል፡፡ በ1996 ዓመተ ምህረት የኢትዮ ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔውን አስተላለፈ፡፡ ሁለቱ ሀገራት ከተፋለሙባቸው ቦታዎች አንደኛዋ የነበረችው ባድመ የኤርትራ ግዛት እንድትሆን ተፈረደ፡፡

ኢትዮጵያ ግን ውሳኔውን ለመቀበል ወታደሮቿን ከባድመ ለማስወጣት አልፈቀደችም፡፡ ኢትዮጵያ የኮሚሽኑን ውሳኔ ተከትሎ የድንበር ማካለሉ ካለ አንዳንድ ቅድመ- እሳቤዎች እንዲሁ ቢተገበር ሊፈጠር የሚችሉ ችግሮችን በመዘርዘር፣ ተጨማሪ ውይይት በሁለቱ ሀገራት መካከል እንዲደረግ ጠይቃለች፡፡

ኤርትራ ግን የኢትዮጵያን ጥያቄ ሳትቀበለው በመቅረቷ፣ የሁለቱ ሀገራት ድንበር ለተጨማሪ 16 ዓመታት የፍጥጫ ስፍራ እንዲሆን ሰበብ ሆነ፡፡

ኤርትራ ባለፉት ዓመታት የአልጀርሱን ስምምነት ተከትሎ የተሰጠው ውሳኔ እንዲከበር ስትጎተጉት ነበር፡፡ ይሄ ባልሆነበት ሁኔታ ሰላም እንደማይኖርም ደጋግማ አሳውቃለች፡፡

የኢትዮጵያ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንበረ ሥልጣኑን በተቆናጠጡ ዕለት አጀንዳዬ ብለው ካወጇቸው ጉዳዮች መካከል ከኤርትራ ጋር ሰላም ማውረድ አንዱ ነበር። ነገር ግን ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አለመግባባት ልትፈታ የምትችለው የአልጀርሱ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ስትፈቅድ ብቻ ነው ሲሉ የኤርትራው መረጃ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል።

ትናንት መደበኛ ስብሰባው ላይ ከትሞ የነበረው የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፤ ኢትዮጰያ ለሁለቱ ሃገራት መፃኢ -ሰላም ሲባል የአልጀርስ ስምምነትን እንደምትቀበል አሳውቋል። ይህም ‘ለሃያ ዓመታት ኢትዮጵያና ኤርትራን በጦርነት ውስጥ ተፋጠው እንዲቆዩ ያደረጋቸውን የድንበር ፍጥጫ መፍትሄ ይሰጥ ይሆን?’ የሚል ተስፋ አዘል ጥያቄ ጭሯል።

ኤርትራ የኢትዮጵያን የአቋም ለውጥ ተከትላ የምትወስደው ርምጃ የሁለቱን ሀገራት የፍጥጫ ዘመን ለማክተምም ሆነ ለማራዘም ወሳኝነት ይኖረዋል፡፡ ምንም እንኳ ጉዳዩን በተመለከተ እስካሁን ከአስመራ ባለሥልጣናት የተሰማ ድምፅ ባይኖርም።

ለተጨማሪ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *