ሃይ ባይ ያጣው ብሔር ተኮር መፈናቀል

በሰሜን ወሎ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙና ከምዕራብ ኦሮሚያ የተፈናቀሉ የአማራ ብሄር ተወላጆች ዘላቂ መፍትሄ እንሻለን ይላሉ።

በራያና ቆቦ፣ ጉባ ላፍቶ እንዲሁም ሀብሩ አካባቢዎች በከተሞች እና በገጠር ቀበሌዎች የተሰባሰቡት ተፈናቃዮች በመቶዎቹ የሚቆጠሩ እንደሆነ ሲዘገብ ቢቆይም፤ በትናንትናው ዕለት የአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን ድርጅት አንድ ሺህ አራት መቶ እንደሚጠጉ አትቷል።ቁጥሩ ከዚህም እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችል ቢቢሲ ያናገራቸው ተፈናቃዮች ይገልፃሉ።የ42 ዓመቱ አቶ ተበጀ ጉበና ገና የስድስት ወይንም የሰባት ዓመት ልጅ ሳሉ በወቅቱ በሰሜን ኢትዮጵያ ተከሰቶ የነበረውን ድርቅ እና ረሃብ ተከትሎ በወቅቱ መንግሥት የሰፈራ መርኃ ግብር አማካይነት ከደምቢ ዶሎ አስራ አምስት ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ገላን መቲ የገጠር ቀበሌ መኖር እንደጀመሩ ይገልፃሉ። ከሃያ ሰባት ዓመት በፊት የመንግሥት ለውጥ በነበረበት ጊዜ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ወደ ትውልድ ቀያቸው ራያ ቆቦ ከመመለሳቸው በስተቀር ህይወታቸውን በሙሉ በዚያው ሲመሩ እንደቆዩ፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት ግን የ”ውጡልን” ድምፆችን መበርታትን ተከትሎ በስጋት ሲናጡ መክረማቸውንም ያስረዳሉ።ስጋቱን ተግ የሚያደርግ ነገር አላገኘሁም የሚሉት አቶ ተበጀ የግብርና ሥራቸውን ትተው ወደቆቦ ከተማ ያመሩት ከስድስት ወራት በፊት እንደሆነ ይናገራሉ።”ታላቅ እና ታናሽ ወንድሞቼ ግን በዚህ ሦስት ሳምንት ውስጥ ነው የመጡት። አባቴ እና የእህቴ ባል እዚያው ናቸው። ለመምጣት እየተዘጋጁ ናቸው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። “እህቴም በእርግጥ ልጆቿን ይዛ መጥታለች።”የራያ እና ቆቦ ወረዳ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ባለሞያ የሆኑት አቶ ሞላ ደርቤ ካለፈው የካቲት ወር አንስቶ የተፈናቃዮቹ ቁጥር እየጨመረ መሄዱን እና ይሄም መስሪያ ቤታቸው በቂ እርዳታ እንዳይሰጥ እየተፈታተነው እንደሆነ ይገልፃሉ።”አሁን ለተፈናቃዮቹ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ብዙም አይደለም” የሚሉት አቶ ሞላ በወረዳቸው ብቻ ያሉ ከምዕራብ ኦሮሚያ የመጡ ተፈናቃዮች ቁጥር ከ510 በላይ መድረሱን ይናገራሉ።ከጥቂት ወራት በፊት ተፈናቃዮቹ 270 ግድም ብቻ የነበሩ ሲሆን፤ ይህንንም ቁጥር ለዞን መስተዳድር በማሳወቅ በቤተሰብ 45 ኪሎ ግራም እህል እና አልባሳትን ሲለግሱ ነበር አቶ ሞላ እንደሚሉት።የተፈናቃዮቹ መበራከት እና የሚሰጠውም እርዳታ በቂ ያለመሆን እገዛ ለማድረግ እንድንንቀሳቀስ ገፊ ምክንያት ሆኖናል የሚሉት ደግሞ በወሎ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት አቶ ያሲን መሃመድ ናቸው።አቶ ያሲን ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ለተፈናቃዮቹ ገንዘብ የሚያሰባስብ ቡድን ያቋቋሙ ሲሆን ይሄውም ቡድን የባንክ ሂሳብ ከፍቶ የዜጎችን እና የተቋማትን ልግስና በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።የተፈናቃዮቹን የዕድሜ እና የፆታ ስብጥር ፈትሸናል የሚሉት አቶ ያሲን እንደሚያስረዱት “ብቻውን ከሆነ እና ሌላ ምንም ቤተሰብ ከሌለው ሰው አንስቶ ስምንት አባላት ያሉትን ቤተሰብ እስካፈራ ሰው ድረስ ተፈናቅሏል፤ አዛውንቶችም አሉበት፣ ሴቶችም አሉበት፣ ትምህርታቸውን ያቋረጡ ህፃናት አሉ።”በወርሃ ጥቅምት ከመቻራ፤ ደምቢዶሎ ስፈናቀል የስምንት ወር ነብሰ ጡር ነበርኩ ስትል ለቢቢሲ የተናገረችው ደግሞ የሰላሳ ዓመቷ ወይዘሮ ፈንታነሽ ሁሴን ናት።”በሰዓቱ ችግር ነበረ፤ ውጡ ሂዱ፤ አገራችንን ልቀቁልን ነበር የሚሉት” የምትለው ፈንታነሽ ያለፉት በርካታ ወራት በየዘመድ ቤቱ በመጠለል እንዳሳለፈቻቸውና ቋሚ መፍትሄ የምታገኝበትን ቀን እንደምትናፍቅ ትገልፃለች።በአነስተኛ ንግድ እና ግብርና ሥራ ላይ ተሰማርታ ለበርካታ ዓመታት ወደኖረችበት ቦታ መመለስ የምትፈልግ አትመስልም፤ “መንግሥት ማረፊያ ቦታ እና መንቃሰቀሻ ገንዘብ” ቢሰጣት ህይወቷን በቆቦ ከተማ እንደ አዲስ ለመገንባት ትፈልጋለች።ሌላኛው ተፈናቃይ አቶ ተበጀም ወደቀደመ ህይወታቸው የመመለስ ጠንካራ ፍላጎት እንደሌላቸው ነው የሚናገሩት፤ የአማራ ክልል መንግሥት “ስለእኛ ብዙ ይቆረቆራል ብዬ ስለማላስብም፤ እርዳታ ለመቀበል እንኳ ሄጄ አልተመዘገብኩም” ይላሉ።ነገር ግን የቆቦ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሻለ ግደይ አስተዳደሩ ለተፈናቃዮቹ ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጥበት አግባብ ላይ እየመከረ መሆኑን ይናገራሉ። “ሁለት አማራጮች ናቸው ያሉት፤ የመጀመሪያው ወደነበሩበት አካባቢ እንዲመለሱ በመንግሥት የተጀመረ እንቅስቃሴ አለ። የሚመለሱት ይመለሳሉ፤ የማይመለሱት ደግሞ እዚህ በዘላቂነት የሚቋቋሙበትን ሁኔታ እያመቻቸን ነው” ይላሉ አቶ ተሻለ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ።መመለስ ወይንም ያለመመለስ ግን የተፈናቃዮቹ ምርጫ መሆኑን አክለው ያስረዳሉ።”ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፤ በአካባቢውም ሰላም እየሰፈነ ስለሆነ ብትመለሱ በነበራችሁበት አካባቢ መስራት ትችላላችሁ የሚል አማራጭ ይቀርብላቸዋል፤ ከዚህ በኋላ በሰዎቹ ፍላጎት ላይ ነው የሚወሰው። ፍላጎት ካላቸው ይሄዳሉ፤ ከሌላቸው ግን በዘላቂነት እዚሁ የሚቋቋሙበት ሁኔታ ላይ እንሰራለን።”የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ባለሞያ የሆኑት አቶ ሞላ መመለስ ለሚፈልጉ ተፈናቃዮች ሁኔታዎችን የሚመቻች ቡድን ወደደምቢዶሎ አካባቢ መንቀሳቀሱን ይናገራሉ።

ምንጭ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *