ብሄር ተኮር ፌደራሊዝሙ ሳይፈርስ ስለ አንድነት ማውራት ከንቱ ድካም ነው

ብሄር ተኮር ፌደራሊዝሙ ሳይፈርስ ስለ አንድነት ማውራት ከንቱ ድካም ነው
ፋሲል የኔዓለም

አሁን ባለው የፌደራሊዝም ስርዓት አንድ ጠንካራ ኢትዮጵያን መገንባት አይቻልም። ላለፉት 26 ዓመታት ክልል ከአገር በልጦ እንዲታይ የተደረገው ቅስቀሳ፣ ቀላል የማይባል የአዲሱ ትውልድ አባላትና “ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ” ሲሉ የነበሩ ከእኔ በፊት የነበሩና የእኔ ትውልድ ሰዎች ሳይቀሩ “ከአገሬ በፊት ክልሌ” እያሉ ሲዘምሩ መስማት እንግዳ አይደለም። ትናንት ባንዲራዋን ታቅፈን ለአንዲት ኢትዮጵያ አብረን የዘመርን ሰዎች፣ ዛሬ “ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያላችሁ አታለቃቅሱ” ብለው ሲናገሩን ስንሰማ፣ እኛን ፖለቲካ የማይገባን ግትሮች ራሳቸውን ደግሞ ፖለቲካ የሚገባቸው ምጡቆች አድርገው ሲቆጥሩ ስናይ ከመገረም ውጭ ሌላ ምን ይባላል? ከወያኔ በሁዋላ በመጣው ትውልድ አልፈርድም። ከወያኔ በፊት የነበሩ ትውልዶች “ክልሌን ወይስ አገሬን?” የሚል አንዱን አስቀድሞ ሌላውን የማስከተል ምርጫ አልነበራቸውም፤ እያንዳንዱ ዜጋ ታማኝነቱ ሁሉ፣ አንድና አንድ፣ ለአገሩ ብቻ ነበር። በጊዜው የነበረው የክፍለ ሃገራት አደረጃጀት የተለያዩ ብሄረሰቦችን የሚያቅፍ በመሆኑ፣ በአንድ ክፍለሃገር ስር ይኖር የነበረ የአንድ ብሄረሰብ ተወላጅ “ከአገሬ በፊት ክፍለሃገሬ” የሚልበት አጋጣሚም ይሁን እድል አልነበረውም። ዛሬ ያለው የክልል አወቃቀር ከብሄር ማንነት ጋር በእጅጉ ተቆራኝቷል። “ክልል ይፍረስ” ብለህ ብትናገር “ብሄርህ ይጥፋ” እንዳልክ ተቆጥሮ ጦር ይሰበቅብሃል። ክልልን የብሄር ማንነት መገለጫ አድርገህ ደግሞ፣ በአንድ አገር ውስጥ “አድልዎ”ን ልታጠፋ አትችልም፤ ያለውን የክልል አስተዳደር እንደያዝክ አድልዎን አጠፋሁ ብለህ የፈለከውን አይነት እርምጃ ብትወስድ እንኳን “ ለብሄሩ አዳልቷል” ከሚል ትችት አታመልጥም ።

ህዝብ፣ ከክልሉ በፊት አገሩን እንዲያስቀድም ከፈለክ አሁን ያለውን ብሄር ተኮር የፌደራል አወቃቀር መቀየር የግድ ይኖርብሃል፤ ይህን ሳትቀይር ጠንካራ አገር እገነባለሁ ብለህ የምታልም ከሆነ ህልምህ ህልም ሆኖ ይቀራል እንጅ ለፍሬ አይበቃም። የፌደራል አወቃቀሩን ሳትቀይር የወልቃይት ጠገዴን፣ የራያን፣ የቁጫንና ሌሎችንም ከማንነትና ከመሬት ጋር የሚነሱ ጥያቄዎችን፣ ጥያቄውን የሚያቀርቡትንና ጥያቄውን የሚቃወሙትን ዜጎች እኩል በሚያረካ መልኩ እፈታለሁ፣ ማለት ዘበት ነው። የአንድ ክልል መሬት የክልሉ ነዋሪዎች ሃብት ብቻ ተደርጎ እየተቆጠረ፣ ክልሎች በድንበር የተነሳ እርስ በርስ ቢጣሉ ሊገርመን አይገባም። የአንዱ ክልል መሬት የአገሪቱ ዜጎች መሬት እንደሆነ ሊታሰብ የሚችለው ከብሄር ማንነት ጋር የተያያዘውን የፌደራል አወቃቀር መለያየት ሲቻል ነው። ሁለቱ ሲለያዩ የሚፈጥረው አደጋ ቢኖርም፣ ከረጅም ጊዜ ጥቅም አንጻር ሲታይ ጉዳቱ አነስተኛና ህዝብን አስቀድሞ በማሳመንና ጥሩ አማራጭ የፌደራል አወቃቀር በማቅረብ የሚስተካከል ነው።

ብሄሮች፣ ሌሎች ብሄሮች የማይነኩባቸው የራሳቸው ብቻ የሆነ የተከለለ መሬት ካልተሰጣቸው በስተቀር መብታቸው አይከበርም የሚል እሳቤ ያለው ሰው፣ የሚያወራው ስለ ብሄሮች መብት ሳይሆን አንድ አዲስ የተለዬ አገር ስለመመስረት ነው። በኢትዮጵያ ድንበር ስር ያለው መሬት ሁሉ የኢትዮጵያን ህዝብ የጋራ ሃብት ነው ብሎ፣ ሌሎች የሰው ልጅ የሚገባውን መብቶች ሁሉ መመለስ ይቻላል። የኢትዮጵያ መሬት ሁሉ የራሳቸው መሬት እንደሆነ እያሰቡ፣ ዜጎች ቋንቋቸው፣ ባህላቸው፣ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው ማድረግ ይቻላል።

መሰረታዊ የሚባሉት የሰው ልጅ መብቶችና አስተዳደራዊ አከላለሎች በቀጥታ የሚያገናኛቸው ነገር የለም። የኦሮምያ አርሶአደር “የኦሮምያ መሬት የኦሮሞ ብቻ ነው” ስለተባለ ከዚህ በፊት በሸዋ ክፍለ ሃገር ስር በነበረበት ጊዜ ከነበረው በተለዬ የሚጠቀመው ነገር የለም፣ እንዲያውም በህወሃት ዘመን ሲጎዳ እንጅ ሲጠቀም አላየንም ። የቦረናን ገበሬ የኦሮምያ ክልል መሬት ያንተ ብቻ ነው ስላልከው መሬቱ አይሰፋለትም፤ ድሮም በሲዳሞ አውራጃ ስር ስለነበረ መሬቱ አልጠበበትም። አሁንም ያለው ድሮ የነበረው ነው። መሬት ከጠበበትም በህዝብ ብዛት የተነሳ እንጅ በሌላ ክልል ስር ስለሆነ አይደለም። የአንድ የኦሮሞ አርሶአደር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መብት ግለሰቡን በሸዋ ክፍለ ሃገር ስር አዋቅሮም ማክበር ይቻላል፤ በድሮዎቹ አወቃቀሮች የነበረው ዋናው ችግር የጋራ መሬት ባለቤትነት ሳይሆን የመብቶች ያለመከበር ችግር ነው። የመሬት ባለቤትነት ችግር ነበር ከተባለም ችግሩ የግል መሬት ችግር እንጅ የጋራ መሬት ችግር አልነበረም። የግል መሬት ችግር ደግሞ ከመንግስት የተበላሸ ፖሊሲ ጋር የሚያያዝ እንጅ ከጋራ መሬት ባለቤትነት ጋር የሚያያዝ አይደለም። ግለሰቦች በቀጥታ የሚጠቀሙት በግል መሬት እንጅ በጋራ መሬት አይደለም፤ የጋራ መሬት ህዝብ በድምር የሚጠቀምበት ሲሆን የግል መሬት ደግሞ አንድ ግለሰብ ብቻ የሚጠቀምበት ነው። “የአማራ ክልል መሬት የአማራ ብቻ ነው” ስለተባለ፣ ግለሰቦች እንደፈለጉ ያገኙታል ማለት አይደለም። አንድ ግለሰብ ከዚህ መሬት ውስጥ ተቆርሶ የሚሰጠው የተወሰነ ብቻ ነው። የተወሰነ መሬት የተሰጣቸውም ያልተሰጣቸውም ዜጎች ሲሰባሰቡ ነው ክልል ወይም አገር እየተባለ የሚሄደው፤ በግለሰብ ደረጃ ከታዬ የመሬት መብት ጥያቄ ተመለሰ የሚባለው መሬትን በፍትሃዊ መንገድ ማከፋፈል እንጅ የክልሉ ህዝብ የራሱ መሬት ተሰጠው እያሉ በመፎከር አይደለም።

ብሄርን ከክልል መሬት ጋር ማያያዙ ተዘዋውሮ በነጻነት የመስራት መብትንም የሚጋፋ ነው። አንድ አርሶአደር ኦሮምያ አካባቢ መኖር ቢሰለቸውና ወደ አማራ ክልለ ሄዶ አንዷን ቆንጆ አግብቶ ጎጆ ለመቀለስ ቢያምረው “ የአማራ መሬት የአማራው እንጅ የኦሮሞው አይደለም ” ተብሎ ይታገዳል፤ በአገሩ በነጻ ተዘዋውሮ ሰርቶና ተዝናንቶ የመኖር ነጻነቱ ተገደበ ማለት ነው። በመብት ማስከበር ስም ዋናውን መብቱን ገደብክበት ማለት ነው። ለሲዳማ ገበሬስ ደስ የሚለው ሳይሸማቀቅ በየተኛውም የአገሪቱ ቦታ ተዘዋውሮ እርሻም ይሁን ሌሎች ስራዎችን ቢሰራ ነው። በ21ኛው ክ/ዘመን የአለም ህዝብ በመሬት መኖር አልበቃው ብሎ ባህርና ህዋ ሲያስስ እየዋለ፣ የአገራችንን ዜጋ በክልል አጥሮ ማስቀመጥ የመብት ጥሰት ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ነው።

እኔ ሆላንድ ውስጥ መብቴ ተከብሮልኝ እኖራለሁ። ሌሎች ኢትዮጵያዊ ጓደኞቼም እንዲሁ፤ ከእነዚህ መካከል አማራዎች፣ ኦሮሞዎች ፣ ሲዳማዎች ወዘተ አሉ። ሆኖም የአማራ ልጆች ሆላንድ ውስጥ “ የአማራ ክልል” የሚባል መብት ተከልሎ ካልተሰጠን መብታችን ተከብሯል ብለን ልንል አንችልም ብለው አንድም ቀን ሰላማዊ ሰልፍ ሲወጡ አላየሁም፤ ኦሮሞዎችም፣ ትግሬዎችም፣ አፋሮችም እንዲህ አይነት ጥያቄ ሲያቀርቡ አልሰማሁም። ጥያቄውን ቢያቀርቡና መሬት ተከልሎ ቢሰጣቸው ተዘዋውረው የመኖርና የመስራት መብታቸው ስለሚገደብ በቅድሚያ የሚጎዱት እነሱ እንጅ ሌላው ህዝብ ሊሆን አይችልም። እነሱም ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ የመሄድ መብት የላችሁም፣ ባላችሁበት ብቻ ነው መኖር የምትችሉት ቢባሉ የመጀመሪያ ተቃውሞ የሚያሰሙት ራሳቸው ይሆናል። ታዲያ እኛ ሆላንድ ውስጥ እንደ ፌንጣ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እየዘለልን መኖር ሲፈቀድልን፣ ለምን አገር ቤት ያለው ወገናችን በተሰጠው አጥር ታጥሮ ይቀመጥ? ሆላንድ ውስጥ ሰው በተሰጠው አጥር ብቻ እንዲኖር ሲገደድ የመብት ጥሰት ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈጠር የመብት መከበር የሚሆነው በምን አመክንዮ ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ የብሄሮች መብት ተከብሯል ለማለት ሰው ተሸንሽኖ በተሰጠው መሬት ውስጥ ተከልሎ መኖሩን እንደ ማሳያ ማቅረቡ ስለመብት አለማወቃችንን ማሳያ ነው። እውነት ለመናገር ለአንድ የወላይታ ገበሬ የደቡብ ክልል መሬት ያንተ ነው ከሚባልና መላው የኢትዮጵያ መሬት ያንተ ነው ከሚባል የትኛው የተሻለ እርካታ እንደሚሰጠው ለመገመት ፊደል መቁጠር አያስፈልግም።

ጽሁፌን የማጠቃልለው ስነሳ ባነሳሁት ሃሳብ ነው። ክልልን ከአገር በላይ አድርጎ እንዲያይ የተሰበከው ወጣት፣ “አንድ ስንዝር መሬት ለሌላ ክልል ተላልፎ እንዲሰጥ አልፈግልም” ብሎ ቢከራከር ሊፈረድበት አይገባም። አንድ የአማራ ወጣት “ወልቃይት የአማራ እንጅ የትግራይ አይደለም” ብሎ ቢከራከር፣ የትግራይም ወጣት በተመሳሳይ መንገድ ሙግት ውስጥ ቢገባ አይፈረድም። ሁለቱም መሬቱ የኢትዮጵያ መሬት እንደሆነ አልተነገራቸውም፤ ለትግሬው ወጣት የተነገረው የወልቃይት መሬት የትግራይ እንጅ የኢትዮጵያ መሬት እንዳልሆነ ነው፤ የአማራው ወጣትም የተነገረው በተመሳሳይ መንገድ ነው፤ በትግራይ መሬት ደግሞ አማራው እንደልቡ እንዲሰራ አይፈቀድለትም። ታዲያ ለክልሉ መሬት ቢሟገት ምን ይገርማል? ስልጣኑን የያዙት ሰዎች ከዘረኝነት አስተሳሰብ ወጥተው ኢትዮጵያዊነት ቢያቀነቅኑ ኖሮ፣ ትውልዱም በኢትዮጵያዊነት ስም ተቀርጾ ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ ብሄርን ማዕከል ያደረገ የድንበር ግጭት ባልተፈጠረ ነበር። አሁን ባለው እውነታ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ማምጣት እጅግ ከባድ ነው። ለጊዜው ራሳችንን ልናታልል እንችላለን፣ መጨረሻችን ግን ላያምር ይችላል። ታዲያ መፍትሄው ምንድነው? ፈርነጆች Back to the basics እንደሚሉት ወደ መሰረታዊው ነገር መመለስ ነው፤ ዜጎች ለኑሮ በሚመቻቸው መንገድ አስተዳደራዊ መዋቅሮችን እንዲዘረጉ መፍቀድ፣ ፍትሃዊ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስርዓት እንዲሰፍን ማድረግ ነው።

አገር በመልካም ንግግር ሊረጋ ይችላል፤ አንድነቱ የሚጸናው ግን ከንግግር ባለፈ ተጨባጭ እርምጃዎች ሲወሰዱ ብቻ ነው። ከእነዚህ እርምጃዎች አንዱ የከሸፈውን ብሄር ተኮር ፌደራሊዝም ተስማሚ በሆኑ ሌሎች መስፈርቶች እንደገና ማዋቀር ነው። አማራ እና አሮሞው፣ አማራና ሶማሊው፣ አማራና ትግሬው፣ አማራ እና ጋምቤላው ወዘተ በኢትዮጵያ ምድር እንደፈለገ ተንቀሳቅሶ ሰርቶና ተዝናንቶ እንዲኖር የሚከልለውን አጥር መንቀል ነው። በአገራችን ውስጥ የድንበር አጥር እንዲኖር መፍቀድ ማለት በነጻነት ተንቀሳቅሰን የመኖር መብታችንን አሳልፈን መስጠት ማለት ነው። አንበሳን እንደልቡ ከሚፈነጭበት ጫካ አውጥተህ በጉሮኖ ( zoo) ውስጥ ስላኖርከው መብቱን አከበርክለት ማለት አይደለም፤ ለአንበሳውስ የሚሻለው አዲሱ የክልል አጥር ሳይሆን እንደፈለገ የሚቦርቅበት መላው ጫካ ነው፤ ለእኛም የሚሻለን መላው አገሩ የእኛ እንደሆነ ስናስብ እንጅ አስተሳሰባችን በክልል ደረጃ ሲታጠር አይደለም። በአንድ አገር ውስጥ ያለው መሬት የሁሉም ህዝብ ሃብት መሆኑን ሳናውጅ ስለአንድ አገርና ስለ አንድ ህዝብ መነጋገር አንችልም። እንደ አንድ አገር ተጠናክረን እንድንወጣ ከተፈለገ ሌሎች ልዩነቶቻችን እንደተጠበቁ ሆነው፣ ቢያንስ “የአገራችን መሬት የሁላችንም ሃብት ነው” በሚለው ላይ የጋራ መግባባት ሊኖረን ይገባል። ይህን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ ብሄርን ማዕከል አድርጎ የተዋቀረውን የክልል ፌደራሊዝም አፍርሶ በሌሎች መስፈርቶች አዲስ ፌደራሊዝም መመስረት ሲቻል ነው።

(ይህ ጽሁፍ በትንሳኤ ሬዲዮ ተላልፏል፣ ጤነኛ የሃሳብ ሙግት እናድርግበት)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *