የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በባለሙያዎች እይታ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የስራ ጉብኝት በማድረግ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል አባላት ጋር ውይይት እያደረጉ ይገኛሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለዓመታት ማህበረሰቡ መንግሥትን ሲጠይቅ ለነበሩ ጉዳዮች ለውጥ ለማምጣት ቃል እየገቡ ነው።

ከሁለት ቀናት በፊት በአዲስ አበባ በሚሊኒየም አዳራሽ “የፍቅር እና የአንድነት ኪዳን” ተብሎ በተሰየመው ኮንፍረንስ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ አገሪቱ ካለችበት ውጥንቅጥ ለመውጣትም አዲስ አቅጣጫ ያስፈልጋል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ማሻሻያ እንደርግባቸዋልን ብለው ካቀረቧቸው ጉዳዮች መካከል፤ የፍትህ ስርዓቱን ነፃና ገለልተኛ ማድረግ፣ የውጪ ምንዛሬ እጥረትን መቅረፍ እና ተዓማኒነት እና እውነተኛ ፉክክር ያለበትን ምርጫ ማካሄድ የሚሉት ይገኙበታል።

የህግ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ያሬድ ለገሰ የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል ትኩረት መስጠት ያለባቸው ሶስት ጉዳዮች አሉ ይላሉ።

እንደ ዶ/ር ያሬድ ከሆነ የፍትህ ስርዓቱን ለማስተካከል መፈጸም ካለባቸው ተግባራት መካከል ቀዳሚ መሆን ያለበት፤ የዳኞችን ቁጥር ከአገልግሎት ፈላጊው ጋር ማመጣጠን ነው። የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል ሌላው ትኩረት መሰጠት ያለበት ሙስናን በተመለከተ እንደሆነ ዶ/ር ያሬድ ይናገራሉ።

እሳቸው እንደሚሉት ሙስናን ከፍርድ ቤት በቀላሉ ማጥፋት አይቻልም። ”እራሳቸውን ከህግ እይታ ውጪ አድረገው የሚያዩ ዳኞች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም” የሚሉት ዶ/ር ያሬድ ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙ ዳኞች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ መወሰድ አለበት ባይ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም ለአቶ ያሬድ የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል ሌላኛው ወሳኝ እርምጃ መሆን ያለበት የፍርድ ቤቶችን የነጻነት ባህል ማሳደግ እና ዳኞች በነጻነት እንዲሰሩ ማስቻል ነው።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በሚሊኒየም አዳራሽ ባደረጉት ንግግር የጸጥታ እና የደህንነት ተቋማት የፖለቲካ ወገንተኝነት እንደሚያሳዩ አምነው፤ እነዚህ ተቋማት ነጻ ሊሆኑ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ የነበሩት ጄነራል አበበ ተ/ሃይማኖት ማሻሻያ ማድረጉ ወሳኝ እርምጃ ነው ይላሉ።

ጄነራል አበበ ”የሃገር መከላከያ ሰራዊት ለህግ እና ህገ-መንግስቱ ብቻ ተገዢ መሆን ሲገባው ‘የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የመጨረሻ ምሽግ ነው፤ ”በአብዮታዊ ዲሞክራሲ መመራት አለበት የሚል መመሪያ ነበረው ይህም ለህገ-መንግሥቱ እና ለኢትዮጵያ ህዝብ የቆመ መሆኑ ቀርቶ ለአንድ ድርጅት ምሽግ ሆኖ ቀርቶ ነበር” ሲሉ ያስረዳሉ።

ጄነራል አበበ ጨምረውም ”ከጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግር እንደተረዳሁት የመከላከያ እና የደህንነት ተቋሙ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ተከትሎ እንዲሄድ ብቻ ይደረጋል ይህም የሚደገፍ ሃሳብ ነው” ይላሉ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ከ25ሺ በላይ ለሆኑ ታዳሚዎች ባደረጉት ንግግር ሌላው የተመለከቱት ጉዳይ የውጪ ምንዛሬ እጥረትን በተመለከተ ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ የውጪ ምንዛሬ እጥረቱ በኢኮኖሚው ላይ እያሳደረ ያለውን ጫና ለመቅረፍ የተለያዩ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን እንደሚወስዱ ተናግረዋል።

የኢኮኖሚው ባለሙያ እና የኢንቨስትመንት አማካሪው አቶ ጌታቸው ተ/ማርያም፤ ”የውጪ ምንዛሬ እጥረቱን ለመቅረፍ እና አስፈላጊ የሆኑ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ለማምጣት እስከዛሬ በተሄደበት መንግድ የሚጓዙ ከሆነ ለእኔ አዲስ ነገር ይፈጠራል ብሎ ማሰብ የማይታሰብ ነው” ይላሉ።

አቶ ጌታቸው ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት እና የውጪ ምንዛሬ እጥረቱን ለመቅረፍ መወሰድ ካለባቸው ተግባራት መካከል ወደ ውጪ የምንልካቸው ምርቶች ጥራት ላይ ትኩረት ማድረግ እና አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን መፍጠር እና መቀላቀል ይገባል ባይ ናቸው።

አዳዲስ የተከፈቱትና በቅርቡ ሲራ የሚጀምሩት ኢንደስትሪያል ፓርኮችንም ቢሆን በተቻለ በፍጥነት ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ መላክ እንዲጀምሩ ማድረግና ከንግድ ጋር የተያያዙ ውስብስብ የመንግስት አሰራሮችን መቅረፍ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው ይላሉ አቶ ጌታቸው፤

ሌላኛው የውጪ ምንዛሪ መጠኑን ያሳድጋል ያሉት የቱሪዝሙን ዘርፍ ነው። የመጀመሪያውና ባለፈው ወር ለሁለተኛ ጊዜ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ደግሞ በዘርፉ ላይ ከፍተኛ ተጽህኖ እያሳደረ ስለሆነ ይህ ጉዳይ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል ሲሉ ያክላሉ ።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ በንግግራቸው ከሁለት ዓመታት በኋላ የሚካሄደውን ምርጭ በሚመለከት ተዓማኒነት እና እውነተኛ ፉክክር ያለበት ምርጫ እናካሂዳለን ማለታቸው ሌላው የበርካቶችን ቀልብ የሳበ ጉዳይ ነበር። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝም መምህር የሆኑት አቶ ናሁሰናይ በላይ ነጻ፣ ገለልተኛ እና ፍትሃዊ ምርጫ እውን እንዲሆን ህዝቡ የሚያምንበት የምርጫ ሂደትና ውጤት ሊኖር ይገባል ይላሉ።

አቶ ናሁሰናይ የምርጫ ቦርድ አጠቃላይ አወቃቀር እንደገና ሊታይና ሊስተካከል ይገባል ሲሉ ከምርጫ በሁዋላም ቢሆን ቅሬታዎችን በአግባቡ ሊያስተናግዱ የሚችሉ ኮሚቴዎች ያስፈልጋሉ በማለት ያክላሉ።

ለተያያዥ ዜናዎች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *