የዩናይትድ ስቴትስ ሴናተር በኢትዮጵያ ዳግም የታሰሩት ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞች እንዲፈቱ ጥያቄ አቀረቡ

በፍሎሪዳ የዩናይትድ ስቴትስ ሴናተር የሆኑት የተከበሩ ማርኮ ሩቢዮ የኢትዮጵያ መንግስት በድጋሜ ለእስር የዳረጋቸውን ጋዜጠኞችን እና የፖለቲካ እስረኞች ነጻ እንዲለቅ ጥያቄ አቀረቡ።

በጋዜጠኝነት ሙያው የተለያዩ አለም አቀፍ ሽልማቶችን ያገኘውን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሌሎች ጦማሪያን እንዲሁም የፖለቲካ መሪዎች መታሰራቸውን የተከበሩ ሴናተር ማርኮ ሩቢዮ ኮንነዋል።

በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ቤት ተሰባስበው በነበሩበት ወቅት በጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር የዋሉት እነ እስክንድር ነጋ መሰባሰባቸው ህገወጥ እንደነበረ እንዲሁም በግቢው ውስጥ ተሰቅሎ የነበረው ሰንደቅ አላማ አገዛዙ ያወጣውን ህግ የጣሰ እንደሆነ በመግለጽ ለእስር እንደተዳረጉ መገለጹ ይታወሳል።

የዩናይትድ ስቴትስ ሴናተር የሆኑት የተከበሩ ማርኮ ሩቢዮ የኢትዮጵያ መንግስት በጋዜጠኞቹ ላይ እንዲሁም በፖለቲካ መሪዎች ላይ  እያደረገ ያለውን እስራት እና የመብት ጥሰት በመቃወም አገራዊና አለምአቀፋዊ  የመብት ተሟጓቾችን መቀላቀላቸው ታውቋል።

ዳግም ወደ እስር ቤት ለመግባት ዝግጁ እንደሆነ  ለዲሞክራሲ እና ለነጻነት የሚደረገውን ትግል ግን ለመተው ዝግጁ እንዳልሆነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ዳግም ከመታሰሩ ከቀናት በፊት መናገሩ ይታወሳል።

የአገሪቷ ጠቅላይ ሚንስትር በመሆን ቃለመሃላ ይፈጽማሉ ተብለው የሚጠበቁት ዶክተር አብይ አህመድ ለዲሞክራሲ፣ ፍትህ፣ እኩልነት እንዲሁም ለነጻነት ሲሉ በየእስር ቤቶቹ እየተሰቃዩ ያሉትን ኢትዮጵያኖች ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ ውሳኔ ማስተላለፍ እንደሚጠበቅባቸው አስተያየት ሰጪዎች እየገለጹ ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪ ንጽኋን ኢትዮጵያኖችን በጠራራ ጸሃይ የገደሉ እና ያስገደሉ የመንግስት ወታደሮችን እንዲሁም ባለስልጣናትን ለፍርድ ማቅረብ ካልቻሉ ዶክተር አብይ ስልጣን ላይ መውጣታቸው እምብዛም ለውጥ እንደማያመጣም የሚናገሩ ተገኝተዋል።Read source

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *